የሱዳን ወታደራዊ ኃይል አል በሺርን በማውረድ ስልጣን መቆጣጠሩን አወጀ

67

ሚያዚያ 3/2011-ሱዳን ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት በወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት ትመራለች፡፡

የሱዳን መከላከያ ሚኒስትር አህመድ አዋድ ቢን አውፍ ሀገሪቱን ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት የሚያስተዳድራት የሽግግር ምክር ቤት መቋቋሙን ይፋ አድርገዋል፡፡

ለሚቀጥሉት ሶስት ወራትም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጸንቶ መውጣቱን ገልጸዋል።

ሌተናንት ጀኔራል አዋድ ኢብን አውፍ በሀገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን በንባብ ባሰሙት መግለጫ ወታደራዊ ኃይሉ ስልጣን መቆጣጠሩን ጠቅሰዋል።

ፕሬዚዳንት አልበሺር ደህንነቱ በተጠበቀ ቦታ ታስረው እንደሚቆዩ ነው የገለጹት።

የሱዳን ህገመንግስት ከስራ ውጭ መሆኑን፣ የሀገሪቱ ድንበሮች መዘጋታቸውን፣ ለ24 ሰዓታት የአየር ክልሏ ከእንቅስቃሴ ውጭ መሆኑን ተናግረዋል።

በቁጥጥር የሚገኙት ፕሬዚዳንት ኦማር ሀሰን አል በሺር በመፈንቅለ መንግስት ወደ ስልጣን ከመጡበት እኤአ 1989 ጀምሮ ላለፉት 30 ዓመታት ሱዳንን መርተዋል።

ሱዳናውያን ካለፈው ታህሳስ ወር ጀምሮ የአል በሺርን አስተዳደር በመቃወም በየጎዳናዎቹ ሰልፍ ሲወጡ ነበር።

አዲስ ህገ መንግስትም በሁለት አመት ውስጥ እንደሚዘጋጅ ታውቋል፡፡

ምንጭ ፡-አልጀዚራና ቢቢሲ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም