በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲና በአካባቢው ማህበረሰብ መካከል ተፈጥሮ የነበረው ግጭት በእርቅ ተፈታ

79
ሚዛን ግንቦት 26/2010 በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲና በሚዛን አማን አካባቢ ማህበረሰብ መካከል ተፈጥሮ የነበረው አለመግባባት በእርቅ ተፈታ፡፡ የቤንች ማጂ ዞን አስተዳደርና ዩኒቨርሲቲው ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር በመሆን በማህበረሰቡ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ትናንት በእርቅ መፍታት ችለዋል፡፡ በእርቅ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች፣ የአካባቢው ማህበረሰብና ዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች ተገኝተዋል፡፡ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወንድሙ ገብሬ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት በዩኒቨርሲቲና በአካባቢው ማህበረሰብ መካከል ግጭት ያልተለመደ ክስተት ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ተፈጥሮ የነበረው መጠነኛ ችግር ፈጥኖ እልባት ባለማግኘቱ ለሚዛን አማን ከተማ መትረፉንና ከተማዋ ለዘመናት የነበራትን የአብሮነት ገጽታ ማጠልሸቱን ገልጸዋል፡፡ “ተማሪዎችም ምክንያታዊ መሆን እንዳለባቸውና ችግር ሲፈጠርም በውይይትና ምክክር የመፍታት ባህልን ማዳበር አለባቸው'' ብለዋል፡፡ በተማሪዎችና በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ከዚህ በፊት የነበረው የልጅና የወላጅነት ስሜት በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አቶ ወንድሙ ተናግረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲውም የተማሪዎችን ጥያቄዎች በአግባቡ በመለየት ፈጣንና ተገቢውን መፍትሔ መስጠት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝደንት ዶክተር አህመድ ሙስጠፋ በበኩላቸው በተፈጠተረው ችግር ዩኒቨርሲቲው እጅጉን ማዘኑን ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በሀገሪቱ ከሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሠላም አምባሳደርነት ሽልማት አሸናፊ እንደነበር አስታውሰው በቀጣይም የቀድሞ ሠላማዊ ገጽታውን ለመመለስ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡ ተፈጥሮ የነበረው ችግር መፈታቱ እንዳስደሰተው የገለጸው ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የሦስተኛ ዓመት ተመሪ ተመስገን ከበደ ነው፡፡ በቀጣይም ተመሳሳይ ድርጊት እንዳይከሰት የበኩሉን ጥረት እንደሚያደርግ ተናግሯል፡፡ የአካባቢው ነዋሪ አቶ አቤል ዶርቴት “ሰሞኑን በአካባቢው ተከስቶ የነበረው ግጭት ያልተለመደና የሚወገዝ ተግባር ነው'' ብለዋል፡፡ የዞኑ አስተዳደርና ዩኒቨርሲቲው ችግሩን ለመፍታትና ያደረጉት ጥረት የሚደነቅ እንደነበር ገልፀው በቀጣይም የግጭት ምንጭ የሚሆኑ ጉዳዮችን አስቀድሞ ለመፍታት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ሥራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የአካባቢው ህብረተሰብና ተማሪዎች የነበራቸው የልጅና ወላጅ ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡ በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲና በአካባቢው ማህበረሰብ መካከል ተከስቶ የነበረውን አለመግባባት ለመፍታት ሲደረግ የነበረውን ጥረት ኢዜአ ሲዘግብ መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም