ከ73 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 71 ኩባንያዎች በማእድን ልማት ዘርፍ መሰማራታቸው ተገለጸ

3958

አዳማ ግንቦት 26/2010 በኢትዮጵያ ከ73 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 71 ኩባንያዎች በማእድን ልማት ዘርፍ መሰማራታቸውን የማዕድን፣ የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሚኒስቴሩ የእቅድ ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክተር አቶ ገረመው ነጋሳ ለኢዜአ እንዳስታወቁት ኩባንያዎቹ የማዕድን ኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው በዘርፉ የተሰማሩት እስከ ሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አጋማሽ ባሉት ጊዜያት ነው።

በእነዚህ ጊዜያት በዘርፉ 7 ቢሊዮን ብር መጠን ያለው ኢንቨስትመንት ለመሳብ ታቅዶ ከ73 ቢሊዮን ብር በላይ የማዕድን ኢንቨስትመንት ማስመዝገብ መቻሉን አስታውቀዋል።

መንግስት የማእድን ባለፍቃዶችን የቀረጥ ነፃ ጥያቄን ተቀብሎ ድጋፍ በማድረጉና ሌሎችም ልማቱን ለማስፋፋት የሚያስችሉ ተግባራትን በማከናወኑ ባለሃብቶች ለዘርፉ ልማት ያስመዘገቡት ካፒታል ከእቅድ በላይ ሊሆን እንደቻል ገልፀዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በልማቱ ውስጥ የሚገኙት ኩባንያዎች በተለያዩ ማዕድናት ፍለጋ፣ ምርምርና ማምረት ላይ መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

ባለፉት ሁለት ዓመት ከዘጠኝ ወር የእቅዱ ትግበራ ጊዜያት 16 ሺህ 223 ኪሎ ግራም ወርቅ፣ 578 ቶን ታንታለምና ከ11 ሺህ ኪሎ ግራም በላይ ጥሬና እሴት የተጨመረበት ኦፓል ተመርቶ ለውጭ ገበያ መቅረቡን ገልጸዋል፡፡

በኩባንያዎችና በባህላዊ ማዕድን አምራቾች ከቀረበው የምርት ሽያጭ 656 ሚሊዮን 804 ሺህ የአሜሪካን ዶላር የውጭ ምንዛሪ መገኘቱን አስታውቀዋል።

የማዕድን፣ የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚንስትሩ አቶ መለስ አለሙ በበኩላቸው በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ቀሪ ጊዜያት የዘርፉን ልማት የሚያፋጥኑ ፕሮጀክቶች ለመሳብ፣ በህግ ማዕቀፍና በተሻለ የአደረጃጀት ለውጥ ስራዎች ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ ከኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ፣ ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከክልል የማዕድን ቢሮዎችና የዘርፉ ተጠሪ ተቋማት ጋር ያለውን ትብብር በማጠናከር የማዕድን መገኛ ቦታዎች ልይታ ስራዎችን ለማስፋፋት ትኩረት መስጠቱን አስታውቀዋል።

በእቅዱ ትግበራ ሂደት በማእድን ልማት የተሰማሩ አካላት ለ380 ሺህ ዜጎች የስራ እድል መፍጠራቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ መንግስትም ከልዩ ልዩ የማእድን ልማቶች 460 ሚሊዮን ብር ገቢ አግኝቷል ብለዋል።

ዘርፉ እንዲያመነጭ ከሚጠበቀው የውጭ ምንዛሪ አንፃር ከምርት እስከ ግበይት እየታዩ ያሉ ህገወጥ የማእድን ልማትና ዝውውር በተቀናጀ ትስስርና ተመጋጋቢነት ለመፍታት ርብርብ እንደሚያስፈልግ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።