የቃሊቲ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር ሊያሻሽል ይገባል -ቋሚ ኮሚቴው

100

አዲስ አበባ ሚያዚያ 3/2011 የአዲስ አበባ የቃሊቲ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በተለይ በገቢ አሰባሰብ ላይ ያለውን ስራ በማቀላጠፍ በቀሪው ወራት ውስጥ ዕቅዱን ማሳካት እንደሚጠበቅበት ቋሚ ኮሚቴው አሳሰበ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢ፣ በጀትና ፋይናስን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ቃሊቲ ጉምሩክ ጽህፈት ቤት የስራ አፈጻጻም የመስክ ምልከታ አድርጓል።

ጽህፈት ቤቱ በዚህ ዓመት ለመሰብሰብ ካቀደው ከ24 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ገቢ ውስጥ በ8 ወራት የተሰበሰበው 16 ቢሊዮን ብር ወይም የአፈጻጸሙን 65 በመቶ በመሆኑ ቀሪውን በቀረው ለማሳካት መረባረብ ያስፈልጋል ብለዋል።

በዚሁ ወቅት ቋሚ ኮሚቴው እንዳሳሰበው ጽህፈት ቤቱ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር ሊያሻሽል ይገባል።

ተቋሙ ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለው ግንኙነት መላላቱን ተከትሎ በገቢው ላይ ተጽእኖ የሚያሳድር በመሆኑ ከግብር ከፋዩ፣ ከአስመጪዎች፣ ከመንግስትና የግል ተቋማት ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር የበለጠ ማጠናከር አለበት።

የኮሚቴው የመስክ ጉብኝት አስተባባሪ ወይዘሮ አበበች ከፈን እንዳሉት፤ ''ጽህፈት ቤቱ እንደ አገር ከተጣለበት ተልዕኮ አንጻር ስራውን በአፋጣኝ ማከናወን ይጠበቅበታል'' ብለዋል።

በተለይ ኮንትሮባንድን በመከላከል ረገድ ከኦሮሚያ አጎራባች ወረዳዎች ጋር በቅንጅት መስራት እንዳለበት አሳስበዋል።

በአገር ደህንነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ የተለያዩ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን መከላከል ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ሲል ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል።

ጽህፈት ቤቱ የኪራይ ሰብሳቢነት፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት እያደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ሰራተኛው የሚያነሳውን ቅሬታ በትኩረት መፍታት ከተቻለ ለተገልጋዩ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያግዝም ጠቁመዋል።

የጉምሩክ መረጃ አያያዝ ለማዘመን የሚደረገው ስራ የበለጠ መጠናከር እንዳለበትና ዘመናዊ የጉምሩክ ቴክኖሎጂዎችን በስራ ላይ ለማዋል የሚደረገውን ጥረት በማጠናከር ቀልጣፋ አገልግሎት የመስጠት ስራ በቀጣይ ሊሰራ ይገባል ሲል ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል።

ቋሚ ኮሚቴው ከጽህፈት ቤቱ በላይ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚሰራም በዚሁ ወቅት ገልጸዋል።

የጽህፈት ቤቱ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አለማየው አንቲቾ በበኩላቸው ከምክር ቤቱ የተሰጡ ግብር መልሶችን መቀበላቸውን ገልጸው ከአቅማቸው በላይ የሆኑትን ጉዳዮች ምክር ቤቱ እንዲያግዛቸው ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም