የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል አገልግሎት የክፍያ ስርአቱን እንደሚያዘምን አስታወቀ

199

ሚያዚያ 3/2011 የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል በአገልግሎት አሰጣጥ ዙርያ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት የአገልግሎት ክፍያ ስርአቱን እንደሚያዘምን አስታወቀ፡፡

አስተያየታቸው ለኢዜአ የሰጡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል አገልግሎት የካርድ ቅድመ ክፍያ ተጠቃሚዎች በበኩላቸው፤ ቀደም ሲል የነበረው የሲስተም መቆራረጥና ረጃጅም ሰልፎች ችግር የተወሰኑ መሻሻሎች ቢኖሩም የኤሌክትሪክ የፍጆታ ክፍያ የታሪፍ ጭማሪ ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል፡፡   

የኤሌክትሪክ ቅድመ ክፍያ አገልግሎት ካርድ በማስሞላት ላይ እያሉ ያገኘናቸው አቶ አብዱራህማን አብዱልፈታህ እንዳሉት  አገልግሎት አሰጣጡ በእለቱ ወረፋ ባይኖረውም አብዛኛውን ግዜ በኔትዎርክ/ሲስተም/ መጥፋት ምክንያት ረጃጅም ሰልፎች እንደነበሩ ነግረውናል።

በሌላ በኩል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተደረገው ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ካሁን በፊት ከሚከፍሉት በእጥፍ የጨመረ ቢሆንም በሀገር ደረጃ የመጣ ሰለሆነ በአግባቡ ከፍለን እየተገለገልን ነው ብለዋል።

ሌላው ተገልጋይ አቶ መሃመድ አደም፤ በአገልግሎት አሰጣጡ ብዙም ቅሬታ ባይኖራቸውም  የዋጋ ጭማሪው ከበፊቱ  ከፍ ያለና  ለመክፈልም ከአቅማቸው በላይ መሆኑን  ይናገራሉ።

“በአንድ ጊዜ የ300 እና 400 ብር ካርድ ሞልተን አንድ ወር ሳይሞላው ያልቃል፤ በርግጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተወሰነ መሻሻል ያለ ይመስላል” ይላሉ፡፡

ወጣት ቃልኪዳን ሽፈራው የበፊቱ አገልግሎት አሰጣጥ በጣም የዘገየ እና ብዙ ሰዓት መጉላላት የበዛበት እንደሆነ ገልጻ፤ ከቅርብ ግዜ ወዲህ መሻሻሎች ታይቷል  ብላለች።

አሁንም ቢሆን “በኔ እምነት ኔትወርክ ወይም ሲስተም ሲጠፋና አገልግሎት የሚሰጡ የሰራተኞች ቁጥር ሲያንስ ወረፋው ይበልጥ ይበዛል፤ ይህ ሊታሰብበት ይገባል” ብላለች፡፡   

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ እንደሚሉት በደንበኞች በርካታ ቅሬታዎች እየተነሳበት ያለው  የኤሌክትሪክ ሃይል ያለማዳረስ ችግርን ለመፍታት የሪፎርም ስራዎች እየተከናወኑ ነው።

ነባር ደንበኞች አስተማማኝ  የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት እንዲያገኙና አዳዲስ ደንበኞችም የኤሌክትሪክ ሃይል አገልግሎት  እንዲያገኙ ማድረግ በዋነኝነት ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተሰራባቸው ያሉ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ለ12 አመታት ሳይቀየር የነበረው የኤሌክትሪክ አገልግሎት የፍጆታ ታሪፍ ጥናት ተደርጎ ከታህሳሰ 1 ቀን /2011 ዓ.ም ጀምሮ ማሻሻያ መደረጉንም ነው አቶ መላኩ ያብራሩት፡፡

ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል፣ ከኢነርጂ ባለስልጣንና ከውሃ መስኖና ኢነርጂ ጋር የተውጣጡ ከፍተኛ ባለሙያዎች ረጅም ግዜ ወስደው  ጥናት በማድረግ  የታሪፍ ማስተካከያ መደረጉንም ተናግረዋል።  

ማሻሻያው ሲደረግ ዛሬ ያለውን የኢነርጂ ዋጋ ታሳቢ ያደረገና የሚመጣጠን ሳይሆን መጠነኛ ማሻሻያ ብቻ መደረጉን ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት።

ተቋሙ የመንግስት ልማት ድርጅት በመሆኑ የሚያደርጋቸው አዳዲስ የኔትወርክ ዝርጋታ፣ ጥገና እና የአስተዳደሩ ወጪ የሚሸፍነው በኤሌክትሪክ ፍጆታ ሽያጭ በሚያገኘው ገቢ መሆኑን የጠቀሱት አቶ መላኩ፤ በነበረው ታሪፍ የሚቀጥል ከሆነ  እየተቆራረጠም ቢሆን የሚገኘውን ሃይል ማድረስ ወደ ሚያዳግትበት ደረጃ ሊደርስ ይችል ብለዋል።

ተቋሙ ገቢውና ወጪው የማይመጣጠን በመሆኑ ባለፉ ሁለት ዓመታት በኪሳራ ይንቀሳቀስ እንደነበረ የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤   ቀደም ሲል ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ የሃይል ፍጆታ ያለውን የህብረተሰብ ክፍል ይደጉም የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ጥናት ዝቅተኛ የሃይል ተጠቃሚን ብቻ የሚደጉም መሆኑን ገልጸዋል።

ታሪፉን የሃይል አጠቃቀም እንደሚወሰነው ያነሱት ዳይሬክተሩ፤ በየወሩ እስከ 50 ኪሎ ዋት የሚጠቀሙ የህብረተሰብ ክፍሎች ቀድሞ የነበረውን የታሪፍ ፍጆታ እንዲከፍሉ፣ እስከ  100 ኪሎ ዋት ለሚጠቀሙ የታሪፉ 75 በመቶ እንዲደጎሙ፣ ከ200 ኪሎ ዋት  በላይ ፍጆታ ያላቸው ድጎማው  እንደማያካትታቸው ነው የጠቆሙት።

እየተስተዋለ የሚገኘው የሃይል መቆራረጥ ያልዘመነ ወይም ያረጀ የኔትወርክ ዝርጋታ ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ የገለጹት አቶ መላኩ፤  ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ፕሮጀክት ተቀርፆ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በመተባበር የሲስተም ዝርጋታ በማከናወን ወደ ተግባር ለመግባት ቅድመ ዝግጅቶች መጠናቀቁን አብራርተዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ህብረተሰቡ አገልግሎቱን በቀላሉ ለማግኘት የፍጆታ ክፍያን በየወሩ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲከፍል ይሆናል ነው ያሉት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም