ተፈናቃዮችን ለማቋቋም መንግስት ትኩረት እንዲሰጥ ተጠየቀ

52

ዲላሚያዚያ 2/2011 ተፈናቅለው በጌዴኦ ዞን የሚገኙ ዜጎችን  መልሶ ለማቋቋም መንግስት  ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ የዞኑ ምሁራን ማህበር አባላት ጠየቁ፡፡

በዞኑ ወቅታዊ ጉዳይ ለመምከር ማህበሩ በዲላ ከተማ ባካሄደው ስብሰባ ላይ ተሳታፊ አባላቱ እንዳሉት ለተፈናቀሉ ዜጎች  አፋጣኝ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ችላ ያሉ አካላት በህግ ሊጠየቁ ይገባል፡፡

ከተሳታፊዎቹ መካከል ዶክተር ተስፍነው በቀለ እንደተናገሩት  ዞኑ ባለፉት ጊዜያት የተቀበላቸው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች በተገቢው ለማስተናገድ ተቸግሯል፡፡

የዞኑን ህዝብና አስተዳደር  ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና መዳረጉን ገልጸዋል፡፡

ተፈናቃዮች በማይመች ሁኔታ ውስጥ ተፋፍገው መጠለላቸው፣ የግልና የአከባቢ ጸዳት አለመጠበቅ፣ እየጣለ ካለው ዝናብ ጋር ተዳምሮ ዜጎችን ለከፋ ጉዳት ሊዳርጋቸው  የሚችል የወረርሽን ምልክቶች መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ከፍተኛ አመራሩ በተለይም የፌዴራል መንግስት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትና የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም በትኩረት እንዲሰራ ጠይቀዋል፡፡

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ  አቶ አሸናፊ በርሶ በበኩላቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች ዕለታዊ ድጋፍ በማድረግ ብቻ በዘላቂነት ማኖር ስለማይቻል መንግስት መልሶ ለማቋቋም ጊዜ ገደብ አስቀምጦ በትኩረት መስራት እንዳለበት አመልክተዋል፡፡

ለጉዳት ለተጋለጡ ዜጎች አፋጣኝ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ለፖለቲካ ትርፍ ሲባል ችግሩን ያድበሰበሱ አካላት ላይ ማጣራት ተደርጎ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ጠይቀዋል፡፡

የጌዴኦና የጉጂ ህዝብ አሁንም ድረስ በጋራ ተከባብረውና ተቻችለው እየኖሩ ቢሆንም የተለያዩ አፍራሽ አጀንዳዎችን ለህዝብ በማቀበል ችግሩን ለማባባስ የሚንቀሳቀሱ አካላት ከድርጊታቸው መቆጠብ እንዳለባቸውም አውስተዋል፡፡

ለዘላቂ ሠላም መረጋጋጥ መንግስት ከሚሰራው በተጨማሪ የህዝብ ለህዝብ ግኑኝነት እንዲዳበር ሁለቱ ዞኖች ተቀራርበው መስራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገዙ አሰፋ በአካባቢው የዜጎች  መፈናቀልን ተከትሎ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን  ገልጸዋል፡፡

ችግሩ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ  ከፌዴራል መንግስት ጀምሮ በተዋረድ ያለው መዋቅር ከአጋር ደርጀቶች ጋር በመቀናጀት የችግሩን መጠን ለመቀነስ ሲሰራ መቆየቱን አንስተዋል፡፡

ታህሳስ 4 /2011 ዓ.ም. አይ ኦ ኤም የሚባል የዕርዳታ ድርጀት በሚደርስበት ጥቃት በአካባቢው እርዳታ ማቅረብ አለመቻሉን ማስታወቁን ተከትሎ ዞኑ ለክልልና ለፌዴራል መንግስት መግለጹን አመልክተዋል፡፡

ለችግሩ አፋጣኝ ምላሽ ባለመሰጠቱ ዜጎች በድጋሚ ተፈናቅለው መምጣታቸውን ለክልሉ አሳውቀው ዘግይቶም ቢሆን ድጋፉ መድረሱን ተናግረዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች ዜጎች ተፈናቅለው ለጉዳት ሲጋለጡ ለችግሩ አፉጣኝ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ችላ ያሉ ተቋማትና አመራሮች ሊጠየቁ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

የጉዳቱ ሁኔታ ከታወቀበት ጊዜ አንስቶ በሀገር ወስጥና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ተውልደ ኢትዮጵያዊያን ላደረጉት ስብዓዊ ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም