በኬኒያ እስር ቤቶች የነበሩ 54 ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው ተመለሱ

119

አዲስ አበባ ሚያዝያ 2/2011 በኬኒያ እስር ቤቶች የነበሩ 54 ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው ተመለሱ።

ዜጎቹ ታስረው የነበረው ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ኬኒያ ሲገቡ በመያዛቸው እንደሆነ ናይሮቢ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

መዳረሻቸውን ደቡብ አፍሪካ ያደረጉ በሞምባሳና ኳሌ በሚገኙ እስር ቤቶች ታስረው የነበሩት እነዚህ ዜጎች ኤምባሲው ከኬንያ ባለሥልጣናት ጋር ባደረገው ማግባባትና ውይይት ከእስር ተለቀው በቅርቡ ወደ አገራቸው መመለሳቸውን አስታውቋል።

ከዚህ በፊት ከኬንያ 145 እና ከማላዊ 34 ኢትዮጵያዊያን ክሳቸው ተቋርጦና ምህረት ተደርጎላቸው ወደ አገራቸው መመለሳቸው ይታወሳል።

ከዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ አንጻር ባለፈው አንድ ዓመት 70 ሺህ ኢትዮጵያዊያን ከተለያዩ አገራት ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ሳዑዲ አረቢያ፣ ግብጽ፣ ታንዛኒያ፣ ሱዳንና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዜጎቹ ከመጡባቸው አገራት መካከል ይጠቀሳሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም