የመቀሌ የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ 450 አመራሮችን አስመረቀ

86

መቀሌ ሚያዚያ 2/2011 በመቀሌ የሚገኘው የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ በጀማሪ አመራርነት ያሰለጠናቸውን 450 አመራሮችን ዛሬ  አስመረቀ።

በ7ኛ ዙር ከተመረቁት አመራሮች መካከል 115ቱ ሴቶች ናቸው።

ከትግራይ ክልል 52 ወረዳዎች የተውጣጡት ሰልጣኞች የህዘባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ/ህወሓት/ እና የትግራይ ህዝብ የትግል ጉዞ፤የአብዮታዊ ዴሞክራሲና የልማት፤የኢትዮጵያ የልማት ፖሊሲና አፈፃፀም በሚሉ ርዕሶች ስልጠና ተሰጥቷቸዋል።

ስልጠናው በመልካም አስተዳደርና በልማት ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ታልሞ ለ48 ቀናት መሰጠቱን የአካዳሚው አመራር ዳይሬክተር አቶ ጎበዛይ ወልደአረጋይ ተናግረዋል።

አመራሮቹ በስልጠናው የጨበጡትን ብቃት ሕዝብን እንዲያገለግሉበት አሳስበዋል።

ከሰልጣኞቹ መካከል የመቀሌ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ባለሙያ አቶ መረሳ ሕሉፍ እንዳሉት በስልጠናው የአመራር ጥበቦችን ቀስመውበታል።ተጨማሪ የአገልጋይነት እልህና ወኔ እንዳሰነቃቸውም ገልጸዋል።

ከትግራይ ደቡባዊ ምስራቅ ዞን የእንደርታ ወረዳ አስተዳደር ባልደረባ አቶ ታረቀን አማረ በበኩላቸው ''በስልጠናው ሁሌም ለሕዝብና ለአገር ልማትና እድገት ግንባር ቀደም ሆኖ መስራት ከአመራር የሚጠበቅ ግዴታ መሆኑን ተሞክሮ አግኝቼበታለሁ'' ብለዋል።

በምረቃው ስነ  ስርዓት ላይ የክልሉ መንግሥትና የህወሓት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ምሁራንና የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም