ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ ያስመዘገበችው እድገት ከአለም ቀዳሚ ነው ተባለ

150

አዲስ አበባ  መጋቢት 2/2011 ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ የጉዞ መዳረሻ ፈጣን እድገት በማስመዝገብ  ከአለም ቀዳሚ መሆኗ ተገለጸ።

የአለም የጉዞና ቱሪዝም ካውንስል እኤአ በ2019 ባወጣው ሪፖርት ኢትዮጵያ ፈጣን እድገት በማስመዝገብ በጉዞ መዳረሻ ከአለም ቀዳሚ ሆናለች።

ከአፍሪካ ደግሞ ርዋንዳ እና ኡጋንዳ ይከተሏታል።

የኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ያስመዘገበው 48 ነጥብ 6 በመቶ እድገት በአገሪቱ ኢኮኖሚ 9 ነጥብ 4 በመቶ ድርሻ ሲይዝ ለ 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች የስራ እድል ፈጥሯል።

አሁን ላይ ከኢትዮጵያ ሰራተኛ ኃይል 8 በመቶ የሚጠጋው በዘርፉ ላይ ተሰማርቶ ይገኛል።

አመታዊ ትንታኔው የተሰራው አለም ዓቀፉን የኢኮኖሚ ሁኔታና የስራ እድል ፈጠራ ተጽእኖን መሰረት በማድረግ 185 አገሮችን በማካተት  መሆኑን ካውንስሉ አስታውቋል።

በጥናቱ መሰረት ዘርፉ ከአለም አጠቃላይ የምርት እድገት 10 ነጥብ 4 በመቶ ድርሻ ሲኖረው 319 ሚሊዮን ሰዎች ቀጥተኛ የስራ እድል አግኝተውበታል።

በዚህም እአአ በ2018 በአለም አቀፍ ደረጃ ከተፈጠረው አጠቃላይ የስራ እድል 10 በመቶ ምጣኔ ይዟል።

የአለም ኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ቢያሳይም የቱሪዝም ዘርፉ እድገት እአአ በ2019 ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ሪፖርቱ አሳይቷል።

የአፍሪካ የቱሪዝምና የጉዞ ዘርፍ እአአ በ2018 ከእስያ ፓስፊክ በመቀጠል ፈጣን እድገት ማስመዝገቡን የካውንስሉ ሪፖርት አስፍሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም