የሰላም ምክር ቤት በየደረጃው ለማቋቋም እየተሰራ መሆኑን የሰላም ሚኒስትሯ አስታወቁ

99

አሶሳ ሚያዝያ 2/2011 ከቤተሰብ እስከ አገር አቀፍ አደረጃጀት ያለው የሰላም ምክር ቤት ለማቋቋም እየተሰራ መሆኑን የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ፡፡

ሚኒስትሯ ትናንት በአሶሳ ከተማ በተካሄደ የሠላም ኮንፍረንስ ላይ እንደተናገሩት ሰላም ከቤተሰብ እስከ አገር አቀፍ ደረጃ ባሉት ደረጃዎች ለማስፈን  ምክር ቤቶቹን ለማቋቋም እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው።

ሚኒስቴሩ የአገሪቱን ሰላም ለማስጠበቅ እያደረገ ባለው እንቅስቃሴ ምክር ቤቱ የሚቋቋምበትን ሰነድ ማዘጋጀቱን አስረድተዋል፡፡

ለዚህም በ100 ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በማሰልጠን ላይ እንደሚገኙ ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡

''ሰላም ስናጣው የምንፈልገው ብቻ ሳይሆን፣ በየዕለት እንቅስቃሴአችን እንደ አየርና ምግብ የሚያስፈልገን የሕይወታችን ምሰሶ ነው። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የራሱ ሰላማዊ ሕይወት ድምር ሰላማዊ አገር እንደሚፈጥር ሊረዳ ይገባል''ብለዋል፡፡

ምክር ቤቱ ትኩረትም ይህንኑ ለማስረጽ እንደሚሰራ ወይዘሮ ሙፈሪያት አመልክተዋል፡፡

''ሕዝብ በምንም መንገድ የሰላም እጦት እንዲሰማው አንፈልግም” ያሉት ሚኒስትሯ፣''መንግሥት ያሳየው ታጋሽነት በሕዝብ ሕይወት ደህንነት ላይ አደጋ ሲመጣ መንግሥት ቀይ መሥመር ይሻገራል” ሲሉም ተናግረዋል፡፡

መንግሥት ቀይ መሥመሩን እንዳይሻገር ኅብረተሰቡ ትብብሩን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል፡፡

ሰላምን ማስፈን የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ ብቻ ሳይሆን፤ ከሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ጋር ማስተሳሰር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

መንግሥት፣የሃይማኖት ተቋማት፣ኅብረተሰቡና ባለድርሻ አካላት በጋራ መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም ሚኒስትሯ አመልክተዋል፡፡

በአሶሳ ከተማ በተካሄደው የኦሮሚያና የቤኒሻንጉል ክልሎች የጋራ የሰላም መድረክ ላይ ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች ተሳትፈውበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም