የገቢዎች ሚኒስቴር በዋና ኦዲተር የተገኘበትን ጉድለት እንዲያስተካክል ምክር ቤት አስጠነቀቀ

271

አዲስ አበባ ሚያዝያ 2/2011 የገቢዎች ሚኒስቴር በዋና ኦዲተር የተገኘበትን የ2009 በጀት አመት ክፍተት በአስቸኳይ እንዲያስተካክል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስጠነቀቀ።

በምክር ቤቱ የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌዴራል ዋና ኦዲተር የ2009 የገቢዎች ሚኒስቴር የኦዲት ግኝት ላይ መሰረት በማድረግ ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የመወያያ ጥያቄዎችን አንስቶ መክሮበታል።

በዋና ኦዲተሩ ግኝት መሰረት የገቢዎች ሚኒስቴር በ2009 ዓ.ም ከጉምሩክ 2 ነጥብ 5፤ ከአገር ውስጥ ገቢ ደግሞ 8 ነጥብ 1 በአጠቃላይ 10 ነጥብ 15 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ እንደነበረበት ማወቅ ተችሏል።

ይሁን እንጂ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በዋና ኦዲተር እንዲሰበሰብ ከተጠየቀው ውስጥ ከጉምሩክ 1 ነጥብ 07፤ ከአገር ውስጥ ገቢ 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን በአጠቃላይ ወደ 2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን አስታውቋል።

በውይይቱ በተለያየ ምክንያት የተወረሱ እቃዎች የአቀማመጥና በወደብ ላይ ረዥም ጊዜ የመቆየት ችግር እንደነበረም በምክር ቤት አባላት ተነስቷል።

ከዚህ በተጨማሪም ከማን እንደሚሰበሰብ ያልታወቀ 48 ሚሊዮን ብር መገኘቱና ህግ በማይፈቅደው መልኩ የተከፈሉ የሰራተኞች የአበል ክፍያ፣ የስራ ግብር ያልተቆረጠባቸው የቤትና ሌሎች ጥቅማጥቅሞች መኖራቸውም ተገልጿል።

አገር ውስጥ የገቡ እቃዎች የቀረጥ ዋጋ ተወስኖባቸው ያልተከፈሉ መኖራቸውና ከጉምሩክ መሰብሰብ ያለበት ገቢ በትክክል እየተሰበሰበ አይደለም የሚሉ ጥያቄዎች ከምክር ቤቱ ተነስተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የቀረጥ ሂሳብ መሰብሰቢያ ደረሰኞች የገቢና ወጪ ወጥ የሆነ ቁጥጥር ስርዓት አለመኖሩ፣ ማሽኖቹ ያለፈባቸው መሆናቸውንና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተቋሙን በጀት በትክክል አለመጠቀም ችግር እንደሚታይበትም ጭምር ተገልጿል።

በመሆኑም ከላይ በተነሱትና ተያያዥ ምክንያቶች አገሪቱ ማግኘት ያለባትን ገቢ እያገኘች አለመሆኑን፤ ይህም የኢኮኖሚ አውታሩ ላይ ጉዳት ስለሚያደርስ በፍጥነት መታረም አለበት ሲል ቋሚ ኮሚቴው አስጠንቅቋል።

አያይዞም ባለበጀት መስሪያ ቤቶች በሙሉ በሁለት ወር ውስጥ የኦዲት ግኝታቸውን አስተካክለው ሂሳባቸውን እንዲዘጉ መጋቢት 16 በምክር ቤቱ  በአፈ-ጉባኤና በፌዴራል ዋና ኦዲተር የተሰጠውን አቅጣጫ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አንስቷል።

የፌዴራል ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በበኩላቸው አገሪቱ በአሁኑ ወቅት ከአገር ውስጥና ከጉምሩክ ማግኘት ያለባትን የቀረጥ ገንዘብ እያገኘች አለመሆኑን አንስተው ችግሩን መንግስት በጥብቅ ሊከታተለው እንደሚገባ አሳስበዋል።

በተለይም የገቢዎች ሚኒስቴርን በተመለከተ አገሪቱ የምትጠቀምባቸው የደረሰኝና የፍተሻ ማሽኖችን ጨምሮ የገቢ መሰብሰቢያ ቴክኖሎጂው ወደኋላ የቀረ መሆኑ ዋነኛ ምክንያት ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በዋና ኦዲተር የተገኙ የኦዲት ግኝቶችን ለማስተካከል የእርምት እርምጃ እየተወሰደ መሆኑንና ብዙዎቹ እየተስተካከሉ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ከንብረት አያያዝ ጋር የተያያዙ ግኝቶችን በማስተካከል ረገድ፣ የተቋሙን በጀት በአግባቡ ከመጠቀምና የጉምሩክና የአገር ውስጥ ገቢን በመሰብሰብ ረገድም ኮሚቴ በማዋቀር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ችግሮቹን ይበልጥ ለመቀነስ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በዘመናዊ ቴክኖሎጂና አሰራር እንዲሁም በብቁ ሰራተኛ የማደራጀት ስራ እንደሚጠይቅ አንስተዋል።

ይህም የተቋሙ ሃላፊነት ብቻ ሳይሆን የምክር ቤቱ፣ የመንግስትና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጭምር ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም