ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ከተመድ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጋር ተወያዩ

277

አዲስ አበባ ሚያዚያ 2/2011 ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑትን ፓራፋይት ኦናንጋ አንያንጌን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

የተመድ ልዩ መልዕክተኛ ከፕሬዚዳንቷ ጋር በነበራቸው ቆይታ በአፍሪካ ቀንድ የሰላም መስፈንን ማረጋገጥ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ መክረዋል።

በተለይም በአፍሪካ ቀንድ ሰላም ለማምጣት እየተደረገ ያለውን ሂደት ለመደገፍ፣ ለቀጠናው ህዝቦች ብልጽግና እንዲሁም ጠንካራ ቀጠናዊ ትብብር ለመመስረት ተመድ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

የሚደረገው ድጋፍ የአካባቢው አገሮችን ፍላጎት ያማከለ እንደሚሆን የገለፁት ልዩ መልዕክተኛው ድጋፉ በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) በኩል እንደሚተገበር አክለዋል።

ልዩ መልዕክተኛው በኢትዮጵያ አገራዊ ለውጥ በሚካሄድበት ወቅት ተመድበው በመምጣታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በሳል አመራርን አድንቀዋል።

በኢትዮጵያ እየተወሰዱ ያሉ የለውጥ እርምጃዎች ለአፍሪካ ቀንድ ብቻ ሳይሆን ለተመድም መልካም አጋጣሚ መሆናቸውን ጠቁመው እርሳቸው ለሚሰሩት ስራ ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውንም አመላክተዋል።

ልዩ መልዕክተኛው በአፍሪካ ቀንድ የአንቶኒዮ ጉተሬዝ ልዩ መልዕክተኛ ተደርገው በቅርቡ የተሾሙ ሲሆን መቀመጫቸውን አዲስ አበባ አድርገው ስራቸውን ያከናውናሉ።