የሕግ የበላይነት እንዲከበር የድርሻችንን እንወጣለን- የምዕራብ ጉጂ ነዋሪዎች

55

ነገሌ መጋቢት 2/2011 አለመግባባቶች በውይይት እንዲፈቱና የሕግ የበላይነት በማስከበር የድርሻቸውን እንደሚወጡ የምዕራብ ጉጂ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

ነዋሪዎቹ በሰላምና በወቅታዊ ጉዳዎች ዙሪያ ትናንት በቶሬ ከተማ ተወያይተዋል፡፡

የገላና ወረዳ ነዋሪ አቶ አበበ ጌሰማ ሕዝቡ "አለመግባባቶችን በውይይት የምንፈታበት ዘመን ባህል አለን" ብለዋል፡፡

በቅርቡ ባህላዊ  ሥርዓቱን በመጠቀም አባገዳዎች ከኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር(ኦነግ) ታጣቂዎች ጋር ባደረጉት ውይይት አብዛኛዎቹ ወደሰላም መመለሳቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በውይይትና በድርድር የማያምኑና የሕግ የበላይነትን የማያከብሩ አካላት አሁንም ንብረት በመዝረፍና የሰው ሕይወት በማጥፋት ላይ እንደተሰማሩ መታዘባቸውን ገልጸዋል፡፡

በዞኑ አንዳንድ አካባቢዎች የሚፈጸሙ የኃይል ጥቃቶችን ማስቆምና የሕግ የበላይነትን ማስከበር የመንግሥት ግዴታና ኃላፊነት እንደሆነ የገለጹት አቶ አበበ "ለተግባራዊነቱ የድርሻችንን እንወጣለን " ብለዋል።

የዚሁ ከተማ ነዋሪ አቶ አየለ ወዴሳ በበኩላቸው አለመግባባቶችን በድርድርና በውይይት መፍታት የተለመደና ነባር ባህላዊ ሥርዓት መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

"የአገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎችና የሃይማኖት መሪዎች በመተባበር አለመግባባቶች ወደ ግጭት ሳያመሩ በውይይት እንዲፈቱ መስራት አለብን" ብለዋል፡፡

የገላና ወረዳ ነዋሪ አቶ ጨሪ ዲዶ በበኩላቸው አለመግባባትን በውይይትና በድርድር በመፍታት የቀደሙ አባቶቻችን የመቻቻል፣ የመከባበርና የአብሮነት ባህል መከተል እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።

በአካባቢው ዘላቂ ሰላም እንዲመጣና የሕግ የበላይነት እንዲከበር ሕዝቡን ለማስተማር ቃል ገብተዋል፡፡

የምዕራብ ጉጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበራ ቡኖ "በዞኑ የልማት ተጠቃሚ ለመሆን ለአካባቢው ሰላም ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል" ብለዋል ።

መንግሥት የመልካም አስተዳደር ችግሮች ከመፍታት ጎን ለጎን የሕግ የበላይነት እንዲከበር እየሰራ መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም