በመጪው እሁድ አገር አቀፍ የጽዳት ዘመቻ እንደሚካሄድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናገሩ

103

አዲስ አበባ ሚያዚያ 2/2011 በመጪው እሁድ መልካም አስተሳሰብን ለመስበክ የሚያግዝ የጽዳት ዘመቻ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች እንደሚካሄድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት ትናንት ማምሻውን በ43ኛው በዓለም አገር አቋራጭ የአትሌቲክስ ውድድር አሸናፊዎች በቤተ-መንግሥት በተዘጋጀው የምስጋና መርሃ-ግብር ላይ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ አሁን አሁን በአገሪቱ በሚከሰተው የጸጥታና ተያያዥ ችግር ሣምንትን ያለ ክፉ ዜና ማለፍ እየከበደ መጥቷል።

ችግሮችን ባሉበት ለማቆምና እንዳይዛመቱ ለማስቻል ቀና ማሰብ ስለሚያስፈልግ በመጪው እሁድ በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች የጽዳት ዘመቻ ይደረጋል ነው ያሉት።

ይህም መጥፎ ስሜትን በመልካም ስሜት ለመተካትና መልካም ለማሰብ የሚያስችል ዘመቻ መሆኑን ጠቁመዋል።

እሁድ ንጋት ከ12 ሰዓት ከ30 እስከ ሁለት ሰዓት ባለው ጊዜ ሁለም ተሽከርካሪዎች እንዲቆሙ በማድረግ በተለይም በአዲስ አበባ ነዋሪዎች በነቂስ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ደግሞ ዩኒቨርሲቲያቸውንና ከተማቸውን እንዲሁም የመንግሥት ሠራተኞችም በጽዳት ዘመቻው ተሳታፊ እንዲሆኑ ጠይቀዋል።

የጽዳት ዘመቻው ቆሻሻን ከአካባቢ መጥረግ እንደሚገባ ሁሉ ከአእምሮም መጥፎና ክፉ ኃሳብን በመጥረግ በመልካም አስተሳሳብ መተካት እንደሚገባ እገረ-መንገዱን ለማስተማር ነው ብለዋል። 

በተለይም ቋንቋን መሰረት ያደረጉ ልዩነቶች በሕብር ውስጥ ያሉ ጌጦች እንጂ የመለያያ ነጥቦች መሆን እንደሌለባቸው ገልጸዋል። 

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሚታዩትን ችግሮች ለመሻገር እርስ በእርስ ተጋግዞ ማለፍ እንደሚገባ ጠቁመው ለዚህም ዜጎች የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም