ውጤታማ አትሌቶች ለተተኪዎቻቸው የስኬት ልምዳቸውን ሊያካፍሉ ይገባል - ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ

158

አዲስ አበባ ሚያዝያ 2/2011 በአትሌቲክስ የስፖርት ዘርፍ ውጤታማ የሆኑ ሯጮች ለተተኪዎች የስኬት ልምዳቸውን ማካፈል አለባቸው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ።

መጋቢት 21 ቀን 2011 ዓም በዴንማርክ አርሁስ ከተማ በተካሄደው 43ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ውድድር ከ63 አገራት ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች አንደኛ በመሆን አጠናቀዋል።

ይህን ተከትሎም ትናንት ማምሻውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በተገኙበት በብሔራዊ ቤተ-መንግሥት የምስጋና መርሃ-ግብር ተካሂዷል። 

በዚሁ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እንዳሉት፤ "በውድድሩ ያገኛችሁት ውጤት ለበርካታ ጊዜያት ያደረጋችሁትን እልህ አስጨራሽ ዝግጅትና ትግል በግልጽ ያሳያል"።

የአትሌቲክስ ውድድድር በባህሪው መተጋጋዝና መረዳዳትን እንደሚጠይቅ ገልጸው ይህንንም በአግባቡ በመተግበር የኢትዮጵያን ሠንደቅ ዓላማ ከፍ አድርጋችኋል ብለዋል።

በአትሌቲክሱ ቀድሞ የነበሩትን ጀግኖች አርአያ በመከተል ለድል መብቃታቸውን ገልጸው "ይህም የኋላውን ከአሁኑ ጋር ማስተሳሰር የመደመር ፍልስፍና ነው" ብለዋል።

በመሆኑም የቀደሙትና የአሁኖቹ ጀግኖች አትሌቶች በጋራ የስኬት ልምዳቸውን ለተተኪዎቻቸው ማስተላለፍ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የአትሌቶቹ ድል አገሪቱ አሁን ካለችበት ችግር ለመውጣት ሌላ የስኬት ስንቅ እንደሚሆን ገልጸው ሁሉም ሕዝብ ከዚህ መማርና መንቃት እንዳለበት ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ወንዞችን ለማልማት የተጀመረውን ፕሮጀክት ለአትሌቶችም የማዘውተሪያ ስፍራ በማቅረብ ሚናው ከፍተኛ በመሆኑ እገዛ ልታደርጉ ይገባል ነው ያሉት። 

በአዲስ አበባ በሁሉም ክፍለ ከተሞች የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችን ለመገንባት ሥፍራዎች የመለየት ተግባር እየተከናወነ ነው ብለዋል።

ለዚህም ደግሞ ከፌዴሬሽኑ ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑን በመግለጽ።

የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽነር አቶ እርስቱ ይርዳ በበኩላችው አገሪቱ በ43ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ውድድር ላመጣችው ውጤት የልዑካን ቡድኑን አባላት አመስግነዋል።

የተገኘው ድል ለሌሎች አትሌቶችና በቀጣይ ለሚካሄዱ ውድድሮች መነሳሳት ለመፍጠር ከፍተኛ ሚና አለው ነው ያሉት። 

በዴንማርክ አርሁስ ከተማ በተካሄደው 43ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ውድድር ኢትዮጵያ 5 የወርቅ፣ 3 የብርና 3 የነሐስ በድምሩ 11 ሜዳሊዎችን በማግኘት ነው በአንደኝነት ያጠናቀቀችው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም