በደቡብ ክልል በሕሙማን እንክብካቤና በሥራ አፈጻጸም ውጤታማ የሆኑ የጤና ባለሙያዎች ተሸለሙ

151

ሆሳዕና ሚያዝያ 2/2011 በደቡብ ክልል በሆስፒታሎች በሕሙማን እንክብካቤና በሥራ አፈጻጸም ውጤታማ የጤና ባለሙያዎች እውቅናና ሽልማት ተቀበሉ።

የክልሉ ጤና ቢሮ ትናንት በሆሳዕና ከተማ ባዘጋጀው ስነ ስርዓት ላይ ለባለሙያዎቹ በነብስ ወከፍ የእውቅና ምስክር ወረቀትና ከብር 4ሺህ 500 እስከ 9ሺህ የሚደርስ ገንዘብ ተሰጥቷል ።

እውቅናና ሽልማት ያገኙት ከአንድ እስከ 39 ዓመት አገልግሎት ያላቸው 50 የጤና ባለሙያዎች ናቸው ።

በተጨማሪም በጡረታ የተገለሉ 16 ባለሙያዎች ሽልማቱ ተበርከቶላቸዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ አቅናው ካውዛ በወቅቱ እንደገለጹት “የሰው ልጅ የትኛውንም ያህል እውቀት ቢኖረው፤ ርህራሄና ሰብዓዊነት ካልታከለበት ውድ የሆነውን የሰውን ልጅ ህይወት ማዳን አይቻልም” ብለዋል፡፡

እውቅናና ሽልማቱን መሰጠት ያስፈለገው ውጤታማ ባለሙያዎች ያሳዩትን መልካም አፈጻጸም እንዲቀጥሉና ሌሎችም የአርአያነታቸው እንዲከተሉ ለማነሳሳትና በሕክምናው ዘርፍ የሚስተዋሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመፍታት እንደሆነ ተናግረዋል።

በዋቸሞ ዩንቨርስቲ ንግስት ኢሌኒ መሐመድ መታሰቢያ ሆስፒታል የህጻናት ስፔሻሊስት ዶክተር ላመስግነው ሞሴ የተሰጣቸው ዕውቅናና ሽልማት በሥራቸው ውጤታማ ለመሆን እንዳነሳሳቸው ገልጸዋል።

“ሩህሩህ፣ ተንከባካቢና ተገልጋይ አክባሪ መሆን ለባለሙያው እርካታ ከመሆኑን በላይ፤ተገልጋዩ በሚያገኘው አገልግሎት ላይ እምነት እንዲኖረው ያስችላል” ብለዋል ።

“አንድ ታካሚ ከሕመሙ መዳን የሚጀምረው ሩህሩህ ሆነንና አክብረን ስናሰተናግደው ነው” ያሉት ደግሞ ከሀዋሳ አደሬ ሆስፒታል ተሸላሚ ሲስተር ተዘራሽ ወርቁ ናቸው፡፡

ዕውቅናና ሽልማቱ ሥራቸውን እንዲወዱት እንዳረጋቸው አስታውቀዋል።