''መንግሥት በዴሞክራሲ ሥም አገር የሚያፈርሱትን አይታገስም''-የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር

116

አሶሳ ሚያዚያ 2/2011 ''መንግሥት በዴሞክራሲ ስም አገር የሚያፈርሱ ግለሰቦችን በዝምታ አያልፍም” ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ አስጠነቀቁ፡፡

በአሶሳ የተካሄደው የቤኒሻንጉል ጉሙዝና ኦሮሚያ ክልሎች የጋራ የሠላም ኮንፍራንስ ትናንት ማምሻውን ተጠናቋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ለማ መገርሣ በኮንፍረንሱ ላይ እንዳመለከቱት የክልሉ መንግሥት በዴሞክራሲ ስም አገር ለመበታተን የሚፈልጉ አካላትን አይታገስም።

መንግሥት የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ ባለበት ኃላፊነት የጥፋት ኃይሎችን እንደማይሸከምም ተናግረዋል።

በቅርቡ በክልሎቹ በተከሰተ ግጭት ብልህነት የተሞላበት እርምጃ ተወስዶ ሰላምና መረጋጋት መስፈኑን ያመለከቱት አቶ ለማ፣ሕዝቡ አንዱ ለሌላው ከለላ በመሆን ያሳየው ኢትዮጵያዊ አንድነትና መደጋገፍ አኩሪ እንደነበር ገልጸዋል።

የአገር መከላከያ ሠራዊትም አካባቢዎቹን ለማረጋጋት  የተጫወተው ሚና ያኮራል ብለዋል፡፡

''ችግሮቻን የሚፈቱት በቀደመ ታሪካችን ሳይሆን፤ በዛሬ ተግባራችን ነው ''ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ፣ ''የማንም መሣሪያ ሳንሆን በመተጋገዝ ለጋራ ሠላምና ልማት አብረን መስራት ይገባናል'' ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በክልሎቹ ግጭት የተሳተፉ ግለሰቦች ለሕግ ለማቅረብ የተጀመረው ሂደት እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡

''ሁለቱ ሕዝቦች የማይጋሩት ጉዳይ የለም'' ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣የሕዝቦቹን ሕይወት ለመቀየር ተቀናጅቶ መሥራትና አገራዊውን ለውጥ ማስቀጠል ያስፈልጋል ብለዋል።

''የኦሮሚያ ክልል የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን ማገዝ እንደ በጎ አድራጎት ሥራ ሊታይ አይገባም'' ሲሉም የሁለቱን ክልሎች ትብብር አስፈላጊነት አመላክተዋል።

ክልሎቹ ማዕድን፣ለም መሬትና የተፈጥሮ ሃብት በማልማት ተጠቃሚ መሆን እንደሚገባቸውም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል፡፡

የሠላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል በበኩላቸው በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች እያጋጠሙ ያሉት ግጭቶች ያለፉት ዓመታት ጉዞ ውጤቶች መሆናቸውን ገልጸው፣በተለይም ወጣቱ አሁን ያገኘውን ነጻነት ከኃላፊነት ጋር በማጣጣም ከግጭቶች መውጣት አለበት ብለዋል፡፡

''አሁን በአገሪቱ ከወሬ ባለፈ ሕዝቡን የሚያዳምጥ መንግሥት አለ''ያሉት ሚኒስትሯ፣ወጣቱ አገሩን እንዲያውቅ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

አንዳንድ የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በክልሎቹ መካከል የተከሰተው ግጭት በሁለቱ ክልሎች ሕዝቦች መካከል እንዳልተከሰተ ገልጸዋል፡፡

ሁለቱ ሕዝቦችን ያላቸውን የደምና የባህል ትስስር በኢኮኖሚ ጭምር ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡

የክልሎቹ መንግሥታት በጋራ ለመሥራት በተስማሙባቸው የልማት ዕቅዶች ላይ ሕዝቡን ማወያየት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

የሃይማኖት መሪዎችና አባገዳዎች ኢትዮጵያዊ አንድነትን በሚያጠናክሩ ተግባራት ላይ እንዲያተኩሩ ጠይቀዋል፡፡

በኮንፍረንሱ ከአንድ ሺህ የሚበልጡ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ የኦሮሚያና አማራ ክልሎች ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም