የኀብረቱ ሰንደቅ ዓላማና መዝሙር ከኢትዮጵያ ጎን ለጎን እንዲሰቀልና እንዲዘመር የሚደነግግ ረቂቅ አዋጅ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ተልኳል

103

አዲስ አበባ  ሚያዝያ 1/2011 የአፍሪካ ኀብረት ሰንደቅ ዓላማና መዝሙር ከኢትዮጵያ ጎን ለጎን እንዲሰቀልና እንዲዘመር የሚደነግግ ረቂቅ አዋጅ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መላኩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።   

አዋጁ የአፍሪካ ኀብረት የተመሰረተበት ቀን ግንቦት 17 / ሜይ 25/ በኢትዮጵያ በቋሚነት እንዲከብር የሚልንም ያካተተ ነው።     

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአዋጁ አስፈላጊነት ዙሪያ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማኀበረሰብ አባላት ጋር ዛሬ ተወያይቷል። 

የአፍሪካ ኀብረት 50ኛ ዓመት ምስረታ በዓል ሲከበር የኀብረቱ አባል አገራት የአፍሪካ ህብረትን ሰንደቅ ዓላማና መዝሙር እንዲሁም የኀብረቱ ቀን ከአገራቸው ጎን ለጎን እንዲተገበር ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል። 

እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ከ1998 ጀምሮ ናሚቢያ የአፍሪካ ኀብረት ሰንደቅ ዓላማ በተለያዩ መንግሥት ተቋማት፣ በትምህርት ቤቶችና በኢምባሲዎች ከራሷ ሰንደቅ ዓላማ ጎን ለጎን በማውለብለብ ቀዳሚ አገር መሆን ችላለች።   

ደቡብ አፍሪካም ከ2015 ጀምሮ ከራሷ ሰንደቅ ዓላማ ጎን ለጎን የኀብረቱን ሰንደቅ ዓላማ ለማውለብለብ ውሳኔ አሳልፋ ተግባራዊ እያደረገች ነው። 

ሚኒስትር ደኤታዋ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ አንድነትና ፓን አፍሪካኒዝም ላይ ቁልፍ ሚና ቢኖራትም ውሳኔውን በመተግበር በኩል መዘግየቶችን አሳይታለች። 

''አገራችንን የመሳሰሉ ለድርጅቱ ምስረታ ቁልፍ ሚና የተጫወቱና የኀብረቱ ልዩ ልዩ አካላት መቀመጫ በአርአያነት የሚጠቀስ ድርብ ኃላፊት አለባቸው'' ያሉት ሚኒስትር ደኤታዋ የጥቁር ህዝቦች ተምሳሌት የሆነችው ኢትዮጵያ እስካሁን ውሳኔውን ተጋብራዊ ማድረግ ነበረባት ብለዋል።

ኀብረቱ ያሳለፈውን ውሳኔ ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው ረቂቂ ተዘጋጅቶ በሚኒስትሮች ምክር ቤት እየታየ መሆኑን አመልክተዋል።   

ረቂቅ አዋጁ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተያዘው ዓመት ይጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።

አዋጁን ሥራ ላይ ለማዋል በሚደረጉ ሂደቶችም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንደሚሳተፉ ጠቅሰው በቀጣይም በአዳማ፣ ሀዋሳ፣ ድሬዳዋ፣ ባህርዳርና መቀሌ ዩኒቨርስቲዎች የማወያየት ሥራዎች እንደሚሰሩ ገልጸዋል።      

ኢትዮጵያ የአፍሪካ አገራት የ2063 አጀንዳ ለማሳካት የተጀመረው እንቅስቃሴ ፍሬያማ እንዲሆን የበኩሏን መወጣቷን እንደምትገፋበትም አክለዋል።    

በሚኒስቴሩ የአፍሪካ ኀብረት ቋሚ መልክተኛ ጽህፈት ቤት ቋሚ ተጠሪ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ በበኩላቸው የአዋጁ መውጣት ትውልዱ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ ያላት ሚና ምን እንደሚመስል እየተገነዘበ እንዲያድግ የማድረግ አዎንታዊ ሚና እንዳለውም አስረድተዋል። 

በአፍሪካ ኀብረት ላይ ኢትዮጵያ ምን አይነት ሚና ነበራት? ለፓን አፍሪካኒዝም እንዴት መነሻ ልትሆን ቻለች? የሚለውን በእውቀት ላይ የተመሰረተ ትውልድ ማፍራት ያግዛል ይላሉ።  

እንደ አምባሳደሩ ገለጻ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገራት ጋር ያላት ትስስርም የበለጠ እንዲጠናከር የውሳኔው ተግባራዊ መሆን የጎላ ጠቀሜታ አለው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም