በአፍሪካ ያላውን እምቅ የውሃ ሃብት በመጠቀም ለወጣቶች የስራ እድል መፍጠር ይገባል

57

አዲስ አበባ ሚያዝያ 1/2011 በአፍሪካ ያላውን እምቅ የውሃ ሃብት በመጠቀም ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ የሚሆኑ ስራዎችን መስራት እንደሚገባ የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ ከአፍሪካ ህብረት፣ ከተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (ዩ ኤን ዲፒ) እና ከጃፓን ኤምባሲ ጋር በመሆን "የውሃ ሃብትን በመጠቀም የስራ እድል ፈጠራ" ላይ ወርክ-ሾፕ ከፍቷል።

የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ስመኝ ውቤ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት በአፍሪካ ከ420 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች ቢኖሩም አህጉሩ አስካሁን የእነሱን እምቅ ችሎታና ክህሎት በአግባቡ መጠቀም አልቻለችም።

ለዚህም የትምህርት ተደራሽነት አናሳ መሆን ፣የፋይናንስ ችግር፣ የስራ እድል ፈጠራ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ መገኘትና በጤና ላይ የሚሰሩ ስራዎች ውስንነት እንደማነቆ የሚጠቀሱ ናቸው።

በመሆኑም ትርጉም ያለው የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትራንስፎርሜሽን ለማምጣት በአፍሪካ ያላውን እምቅ የውሃ ሃብት በመጠቀም ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ የሚሆኑ ስራዎችን መስራት ይገባል ብለዋል።

የውሃ ሃብትን ተንከባክቦና በአግባቡ ተጠቅሞ ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ማዋል ጠንካራና ዘላቂ የሆነ የከተማ አድገት ለማምጣት እንደሚረዳም  ጠቅሰው፤ በዚህም የአሜሪካ፣ የቻይና፣ የከናዳና የጀርመን ተመሞክሮና ልምድ መውሰድ ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ያላትን የውሃ ሃብት ለመጠቀም ብቻ ሳይሆን የወንዞች ዳርቻን ለማልማት ፕሮጀክት ቀርፃ እየተንቀሳቀሰች ሲሆን ይህ ወርክሾፕ አገሪቷ የውሃ ሃብቷን ለመጠቀም ያላትን ፍላጎት አውን ለማድረግ የማስቻል አጋጣሚ አለው ሲሉም አስታውቀዋል።

የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮገራም (ዩ ኤን ዲፒ) ሁሉን አቀፍ እድገትና ዘላቂ ልማት ቡድን መሪ ሚስተር ማንሱር ናዲጊ በበኩላቸው  በአፍሪካ ወጣቶች ያላቸውን እምቅ አቅም ከመጠቀም ይልቅ አንደ ጥፋት ኃይል የመፈረጅ ረዥም ጊዜ ያስቆጠረ ዝንባሌ መኖሩን ተናግረዋል።

ይህን ፍረጃና ትርክት በመቀየር ወጣቶችን በአህጉሩ ባለው የውሃ ሃብት የስራ እድል ተጠቃሚ ማድረግ ተገቢ እንደሆነ ጠቁመው ይህም ወጣቶችን በማብቃት አህጉሩ ያሰቀመጠውን የአጀንዳ 2063 ለማሳካት ያስችላል ሲሉም ገልጸዋል።

በአፍሪካ ህብረት የጃፓን ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ፉሚዮ ሺሚዙ ደግሞ  የአፍሪካ ወጣቶች ልማትን ለማረጋገጥና ስኬትን ለመጎናጸፍ ትምህርት ላይ ኢንቨስት ማድረግ ዋናውና ቁልፍ ተግባር መሆን አለበት ሲሉ ተናግረዋል።

የአፍሪካ ወጣቶችን ክህሎትና ብቃትን በትምህርት ማብቃት የኢኮኖሚ እድገት እንዲረጋገጥ ብቻ ሳይሆን አፍሪካ የምትፈልገውን የኢኮኖሚ ውህደት ለማምጣትና በዓለም አቀፉ ደረጃ በኢኮኖሚ ተወዳዳሪ የሆኑ ምርቶችን ለማምረት ወሳኝ ሚና ይጫወታል።

በመሆኑም ጃፓን የአፍሪካ ወጣቶች በአህጉሩ ያለውን እምቅ አቅም በተለይም የሐይቅና የወንዞች አቅም ተጠቅመው ውጤታማ እንዲሆኑ የጀመረችውን ድጋፍና እገዛ አጠናክራ ትቀጥላለች ሲሉ አረጋግጠዋል።

ወርክ-ሾፑ ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የመጡና በስራ ፈጠራ ላይ የተሰማሩ ወጣቶችን ያሳተፈ ሲሆን የፊታችን ሀሙስ ይጠናቀቃል ተብሎም ይጠበቃል።

በወርክ ሾፑ በስራ እድል ፈጠራ፣ በስራ እድል ፈጠራ አማራጮችና በቴክኖሎጂ ፈጠራና በውሃ ሃብት አጠቃቀም ላይ ውይይትና የልምድ ልውውጥ ይደረጋል ተብሎም ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም