የህዝቦች ወንድማማችነትና የአብሮነት መልካም እሴቶች በአፍራሽ ሃይሎች ተልዕኮ አይደናቀፍም-ኦዲፒ

73

አዲስ አበባ ሚያዚያ1/2011 የህዝቦች ወንድማማችነትና የአብሮነት መልካም እሴቶች በአፍራሽ ሃይሎች ተልዕኮ አይደናቀፍም ሲል የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፓርቲ(ኦዲፒ) ገለጸ።

ኦዲፒ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው ሰሞኑን በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደርና በክልሉ በሰሜን ሸዋ ዞን አንዳንድ ወረዳዎች በነዚህ ሃይሎች ቀስቃሽነት ግጭቶች መከሰታቸውና በሰው ህይወት፣ በአካልና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን አስታውቋል።

ኦዲፒ በግጭቱ ለጠፋው የሰዉ ህይወት፣ ለደረሰው የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለፀ በግጭቱ ውድ ህይወታቸውን ያጡ ወገኖች ፈጣሪ ነብሳቸውን በገነት እንዲያኖር እየተመኘ ለተጎጂ ቤተሰቦችም መፅናናትን ተመኝቷል።

አንዳንድ የፖለቲካ ሃይሎች የዴሞክራሲ ምህዳሩን በማስፋት የተፈጠረዉን ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው በሰለጠነና በሰላማዊ መንገድ የፖለቲካ አጀንዳቸውን ከማራመድ ይልቅ የብሄር ጽንፈኛ አስተሳሰብን አንግበው በመነሳት፣ ህጋዊና ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እንቅስቃሴን ከህገ ወጥና የግጭት መንገድ ጋር እያጣቀሱ እየተንቀሳቀሱ መሆኑ ታይቷል ይላል መግለጫው።

ጽንፈኛ የፖለቲካ ሃይሎች ከከሰሩ የፖለቲካ ሃይሎች ጋር በመቀናጀትም ለዘመናት በአብሮነት እና በፍቅር የኖረን ህዝብ ሊያቃቅሩ ብሎም ሊያጋጩ የሚችሉ አጀንዳዎችን በመቅረጽ ህዝብን ከህዝብ ጋር በማጋጨትና ንፁሃን ዜጎችን በእሳት በመማገድ ሀገራችን ከማትወጣበት የግጭት አዙሪት ውስጥ በመክተት የለውጥ እንቅስቃሴውን ማደናቀፍ ዋነኛ ዓላማቸው አድርገው በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኙም ገልጿል።

የግጭቱን ጠንሳሾች እና ተሳታፊዎች ለህግ ለማቅረብ በህግ አስከባሪ አካላት የሚደረገዉን የህግ የበላይነት የማስከበር እንቅስቃሴ እንዲሳካም ፓርቲው ያልተቆጠበ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጿል፡፡

በመሆኑም በአገራችን የቆየውን የህዝቦች ወንድማማችነትና የአብሮነት መልካም እሴቶች በአፍራሽ ሃይሎች ተልዕኮ እንደማይደናቀፍ በመግለጽ ህዝቡን በነዚህ  ኃይሎች ከሚረጩ አፍራሽ ተልዕኮዎች ራሱን እንዲጠብቅ አሳስቧል መግለጫው።

የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል።

በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ከኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዲፒ) የተሰጠ መግለጫ

በአገራችን ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የፖለቲካ ምህዳሩ ሰፍቶ ማንኛዉም አካል በነጻነት የመደራጀት፣ የፈለገዉን የፖለቲካ አጀንዳ በሰላማዊ መንገድ እንዲያራምድ፣ የሀገራችን ህዝቦች ለዘመናት የታገሉለትና ዉድ መስዋዕትነት የከፈሉበት እዉነተኛ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እዉን እንዲሆን በርካታ ስራዎች በመሰራት ላይ ይገኛሉ፡፡

በዚህ ረገድ ተስፋ ሰጪ ተጨባጭ ዉጤቶችም በመመዝገብ ላይ ናቸዉ፡፡ ሆኖም አንዳንድ የፖለቲካ ሃይሎች ዴሞክራሲ ምህዳሩን በማስፋት የተፈጠረዉን ምቹ ሁኔታ ተጠቅመዉ በሰለጠነና በሰላማዊ መንገድ የፖለቲካ አጀንዳቸዉን ከማራመድ ይልቅ የብሄር ጽንፈኛ አስተሳሰብን አንግበዉ በመነሳት፣ ህጋዊና ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እንቅስቃሴን ከህገ ወጥና የግጭት መንገድ ጋር እያጣቀሱ እየተንቀሳቀሱ መሆኑ ታይቷል፡፡

እነዚህ ጽንፈኛ የፖለቲካ ሃይሎች የከሰሩ የፖለቲካ ሃይሎች ጋር በመቀናጀት ለዘመናት በአብሮነት እና በፍቅር የኖረን ህዝብ ሊያቃቅሩ ብሎም ሊያጋጩ የሚችሉ አጀንዳዎቸን በመቅረጽ ህዝብን ከህዝብ ጋር በማጋጨትና ንፁሃን ዜጎችን በእሳት በመማገድ ሀገራችን ከማትወጣበት የግጭት አዙሪት ዉስጥ በመክተት የለዉጥ እንቅስቃሴዉን ማደናቀፍ ዋነኛ አላማቸዉ አድርገዉ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡

ሰሞኑንም በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደርና በክልሉ በሰሜን ሸዋ ዞን አንዳንድ ወረዳዎች በነዚህ ሃይሎች ቀስቃሽነት ግጭቶች መከሰታቸዉና በሰዉ ህይወት፣በአካልና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ይታወቃል፡፡

ኦዲፒ በግጭቱ ለጠፋዉ የሰዉ ህይወት፣ የአካል ጉዳት እና የንብረት ዉድመት የተሰማዉን ጥልቅ ሀዘን እየገለፀ በግጭቱ ዉድ ህይወታቸዉን ያጡ ወገኖች ፈጣሪ ነብሳቸዉን በገነት እንዲያኖር እየተመኘ ለተጎጂ ቤተሰቦችም መፅናናትን ይመኛል፡፡ የጥፋት ድርጊቱንም አጥብቆ ያወግዛል፡፡

በህዝብ ደም የሚነግዱ የፖለቲካ ቁማርተኞች የተፈፀመዉ ጥፋት በየትኛዉም መልኩ ተቀባይነት የሌለዉና ማንኛዉንም ህዝብ የማይወክል መሆኑን አዲፒ ይገነዘባል፡፡

የግጭቱን ጠንሳሾች እና ተሳታፊዎች ለህግ ለማቅረብ በህግ አስከባሪ አካላት የሚደረገዉን የህግ የበላይነት የማስከበር እንቅስቃሴ እንዲሳካ ፓርቲያችን ያልተቆጠበ ድጋፍ ያደርጋል፡፡

ፓርቲያችን ኦዲፒ የተፈጠረዉን ችግር ለማረጋጋት እና ተመሳሳይ ችግር ዳግም እንዳይከሰት ለመከላከል ከአማራ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) እና ከአማራ ክልላዊ መንግስት ጋር በመቀናጀት በመስራት ላይ ይገኛል፡፡

በእኩይ የጥፋት ድርጊት የሰከሩ ሀይሎች ሰሞኑን የለኮሱት የጥፋት እሳት የህዝብ ለህዝብ ግጭት በማስመሰልና ችግሩ በኦሮሚያ ክልል እንዲስፋፋ በማድረግ ለዘመናት በወንድማማችነትና በመተሳሰብ በሰላም አብረዉ እየኖሩ ያሉ የኦሮሞና የአማራ ወንድማማች ህዝቦችን በግጭት እሳት በመማገድ ጊዜያዊ የፖለቲካ ትርፍ ለማጋበስ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኙ ታዉቋል፡፡

በሰላም አብሮ የሚኖሩትን ወንድማማች ህዝቦች ለማጋጨት የሚደረግ ማንኛዉም ሙከራና ድርጊት ህዝቦች ለዘመናት ባካበቱት የአብሮነት ዕሴት እና የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ ሴራዉን ለማክሸፍ ኦዲፒ ዛሬም እንደ ትናንቱ ጠንክሮ ይሰራል፡፡

በዚህ አጋጣሚም የኦሮሞ ህዝብ በተለመደዉ የአቃፊነት ባህሉ ወንድም ከሆነዉ የአማራ ህዝብ እና ከሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ጋር ያለዉን አብሮነት በማጠናከር፣ በክልሉ በህዝቦች መካከል ግጭት ለመፍጠር የሚደረጉ የጥፋት ሀይሎችን ሴራ ለማጋለጥ እና ለማክሸፍ እንዲንቀሳቀስ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

ኦሮሚያ የሁሉም ኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ቤት እንደሆነች ኦዲፒ በጽኑ ያምናል፡፡

በክልላችን የሚኖሩ ብሄር ብሄረሰቦች አሁን የደረሰንበት የለዉጥ ምዕራፍ ላይ እንድንደርስ ከኦሮሞ ህዝብ ጋር አንድ ሆነዉ ከመሪዉ ፓርቲ ኦዲፒ ጎን ተሰልፈዉ ታግለዋል፤ ዉድ መስዋዕትነትም ከፍለዋል፡፡

ፓርቲያችን ኦዲፒ ለዚህም ታላቅ አክብሮት እንዳለዉ በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ ይወዳል፡፡ በክልላችን ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በሰላም፣ በእኩልነት፣ በወንድማማችነት እና በነጻነት እንዲኖሩ ችግሮች ሲከሰቱም ከአሁን ቀደም እየፈታናቸዉ በመጣንበት መንገድ እየተወያየን መፍትሄ እየሰጠን ለመሄድ ዝግጁ መሆናችንና ለጽንፈኛ እና ለከሰሩ የፖለቲካ ሃይሎች የሚከፈት በር እንደማይኖር፤ ለዚህም ፓርቲያችን መላዉን የክልሉን ህዝብ ከጎኑ በማሰለፍ ከማንኛዉም ጊዜ በበለጠ ትግሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ለማረጋገጥ እንወዳለን፡፡

ፓርቲያችን ኦዲፒ የህዝቦች ወንድማማችነት፣ የኢትዮጵያን አንድነት እና የለዉጡን እንቅስቃሴ ለመገዳደር የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ እና የከሰሩ የፖለቲካ ሃይሎችን ከመላዉ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን እንዲሁም ከለዉጥ ኃይሎች ጋር በመተባበር በጽናት የሚታገላቸዉ መሆኑን ደግመን እናረጋግጣለን!

የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፓርቲ

ሚያዚያ 1/2011

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም