በሶስት ዞኖች ከአንድ ሚሊዮን ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ሰብል እንደሚለማ ተገለጸ

54
ፍቼ/ አርባምንጭ/ደብረብርሃን ግንቦት 25/2010 በኦሮሚያ፣ በአማራ እና በደቡብ ህዝቦች ክልሎች በሚገኙ ሶስት ዞኖች ከአንድ ሚሊዮን ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የተለያየ ሰብል እንደሚለማ ተገለጸ፡፡ በኦሮሚያ ሰሜን ሸዋ ዞን ከ 455 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት በአዝርእት፤ በስራስር፣ በአትክልትና በቅመማ ቅመም ሰብል ለመሸፈን የሚያስችል የማሳ ማለስለስና ማዘጋጀት ስራ ተጀምሯል። በዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት የአዝርእትና ኤክስቴንሽን ቡድን መሪ አቶ ደረጄ ኤጀታ ለኢዜአ እንዳሉት በተያዘው በጀት በተጀመረው የእርሻ ስራ ከ 350 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተፈጥሮ ማዳበሪያ የማለስለስና አፈሩን የመገልበጥ ስራ ተከናውናል፡፡ በምርት ዘመኑ ከሚለማው መሬት ከ75 በመቶ በላይ የሚሆነው በመስመር ለመዝራት ታቅዷል። "ይህም በዞኑ ከዚህ በፊት ይገኝ የነበረውን አጠቃላይ ምርት መጠን ከሰምንት ሚሊዮን ኩንታል ወደ 16 ሚሊዮን ኩንታል ለማሳደግ የታለመ ነው" ብለዋል። ዋና ዋና ሰብሎች ምርታማነትን በሄክታር ከ20 ኩንታል ወደ 27 ኩንታል ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡ ለዚህም አርሶ አደሮች ካሁን በፊት የታዩ ጉድለቶችን በማረም የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችንና ቴክኖሎጂዎችን በአግባቡ ስራ ላይ እንዲያውሉ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን የሰብል ልማት ባለሙያ የሆኑት አቶ ተስፋዬ  ፈዬ ተናግረዋል፡፡ በግራር ጃርሶ ወረዳ የቶርባን አሼ ቀበሌ አርሶ አደር ባልቻ ሁንዴ በሰጡት አስተያየት ምርታቸውን ለማሳደግ የተፈጥሮና ዘመናዊ ማዳበሪያ ለመጠቀም ከወዲሁ መሬታቸውን ማለስለሳቸውን ገልጸዋል። ከዚህ ቀደም በሁለት ሄክታር መሬታቸው ላይ ያገኙ የነበረውን 21 ኩንታል ጤፍ በእጥፍ ለማሳደግ የተሻሻሉ አሰራሮችንና ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀሙ በባለሙያዎች በተሰጣቸው ምክር መሰረት ተግባራዊ እንደሚያደርጉም አመልክተዋል፡፡ በኩዩ ወረዳ የሚልኬሳ ቀበሌ አርሶ አደር  ታደሰ ቱጁባ እንዳሉት በባለሙያ የተሰጣቸውን ትምህርት በመጠቀም  በምርት ዘመኑ  ምርታማነታቸውን ለማሳደግ እየሰሩ ነው። "ሶስት ሄክታር የእርሻ መሬቴን  ሙሉ በሙሉ በመስመር የመዝራት ዘዴን ተከትዬ አርሻለሁ" ያሉት ደግሞ  የዚሁ ቀበሌ አርሶ አደር ማርሸት ጎንፋ ናቸው። ካለፉት ዓመታት  የተሻለ ምርት ለማገኘት የማሳቸውን  ለምነት የሚጨምሩ ስራዎችን  እያከናወኑ ናቸው፡፡ በዘንድሮው መኸር እርሻ 177 ሺህ አርሶ አደሮች እንደሚሳተፉና ለግብዓት መግዥ 11 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉን ከዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በአማራ ሰሜን ሸዋ ዞን በ2010/2011 የመኸር ወቅት ከ 509 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ ገልጿል፡፡ ከ 653 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያም ለአርሶ አደሩ እየቀረበ መሆኑም ተመልክቷል፡፡ በመምሪያው የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ዘሩ ገረመው እንደገለጹት በምርት ዘመኑ አርሶ አደሩ እስካሁን 421 ሺህ 121 ሄክታር መሬት አርሶ ለዘር አዘጋጅቷል፡፡ ቀሪ መሬት በቂ እርጥበት የሚፈልግ በመሆኑ በቀጣይ የሚታረስ ይሆናል፡፡ ከታረሰው መሬት ውስጥም ከ 20 ሺህ 781 ሄክታር በማሽላ፣ በገብስ፣ በተልባ፣ በበርበሬ፣ በበቆሎ፣ በዳጉሳና በስንዴ ዘር ተሸፍኗል፡፡ በእርሻ ስራውም 123 ሺህ 353 አርሶ አደሮች መሳተፋቸውን የጠቀሱተ አቶ ዘሩ ከመካከላቸወም ከ14 ሺህ በላይ ሴቶች እንደሚገኙባቸው ተናግረዋል፡፡ 653 ሺህ 507 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለምርት ዘመኑ ለማቅረብ ተዘጋጅቶ በእጅ ክፍያና በብድር ስርጭቱ እየተካሄደ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በመምሪያው የግብርና ግብዓት አቅርቦት ስርጭትና የገጠር ፋይናስ አገልግሎት ቡድን መሪ ወይዘሮ ሙሉ ዘገየ ናቸው፡፡ 13 ሺህ ኩንታል የሚጠጋ የተለያየ ሰብል ምርጥ ዘር ለማቅረብም ለማቅረብ ዝግጅት ላይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪ ከ3 ሚሊዮን ሜትሪክ ኩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተዘጋጅቶ እስካሀን ከዚህ ውስጥ ከ2 ሚሊየን ሜትሪክ ኩብ የሚበልጥ ጥቅም ላይ መዋሉንም ጠቅሰዋል፡፡ በባሶና ወራና ወረዳ ዘንደጉር ቀበሌ አርሶ አደር አምዴ ኃይለማሪያም በሰጡት አስተያየት በመኸር የሚያለሙት አንደ ሄክታር መሬት እንዳላቸውና በዚህመ ስንዴ፣ ጤፍ፣ ባቂላ ፣ ሽምብራ በዘር ለመሸፈን የአካባቢውን ምርጥ ዘር ማዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡ "ማዳበሪያ በምክረ ሀሳቡ መሰረት በስፋት ለመጠቀም ብድር መመቻቸቱ ያለነን መሬት ካለገደብ በመጠቀም ለማልማት ተጠቃሚ እንድንሆን ያስችለናል" ብለዋል፡፡ ስምንት  ጥማድ መሬታቸውን  በተለያየ ሰብል ለማልማት በቂ ማዳበሪያ መግዛታቸውን የተናገሩት ደግሞ የሞረትና ጅሩ ወረዳ  አርሶ አደር ቦጋለ ለማ  ናቸው፡፡ በተጨማሪም  አስር  ኩንታል ፍግ ማዘጋጀታቸውንና ለሚያለሙት ሰብል አንድ ኩንታል ምርጥ ዘር ማዘጋጀታቸውን አርሶ አደሩ ጨምረው ገልጸዋል፡፡ በምርት ዘመኑ በዞኑ ከሚለማው መሬት ከ16 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በጋሞጎፋ ዞን ከ160 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ እየሰራ መሆኑን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ ገልጿል፡፡ የመምሪያው ኃላፊ አቶ ማጌሶ ማሾሌ እንዳሉተ በመኸሩ  ከሚለማው ሰብል ውስጥ  በቆሎ፡ ገብስ፣ ማሽላና ቦሎቄ ይገኙበታል፡፡ አርሶ አደሩ ሙሉ አቅሙን በእርሻ ስራው ላይ እንዲያሳልፍ በልማት ቡድንና በአንድ ለአምስት ትስስር በማደራጀት በትኩረት እንደሚሰራና የማዳበሪያና ምርጥ ዘር ጥመርታውን በአግባቡ እንዲጠቀም የፈጻሚ ማዘጋጃ መድረክ በሁሉም ወረዳዎች መካሄዱን ጠቁመዋል፡፡ "በ2010/2011 የምርት ዘመን የመኸር እርሻ ከ82 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ለማሰራጨት ታቅዷል" ያሉት ደግሞ በመምሪያው የግብርና ግብአት ሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ያያ ዳልቦ ናቸው፡፡ የአርሶ አደሩ ከቤት ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ገበያ ተኮር ሰብል እንዲያመርት ትኩረት መሰጠቱን አመልክተዋል፡፡ ለምርት ዘመኑ ከ82 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር እየተሰራጨ ነው ተብሏል፡፡ በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ የቆላ ሼሌ ቀበሌ አርሶ አደር ይልማ ቆንስል እንዳሉት አምና ከመኸር እርሻ ሙሉ ፓኬጅ በመጠቀም ካለሙት አንድ ሄክታር ማሳ 61 ኩንታል በቆሎ አምርተዋል፡፡ ከምርቱም ሽያጭ ከ50 ሺህ ብር በላይ ገቢ አግኝተዋል፡፡ ዘንድሮ ከጋሞጎፋ ዞን "ህብረት ፍሬ ዩኒየን" ጋር በመሆን በማሳቸው የበቆሎና ስንዴ ዘር ብዜት በማከናወን የምርጥ ዘር ወጪ  እንደቀነሰላቸው አርሶ አደሩ ተናግረዋል፡፡ በዞኑ በመኸሩ ወቅት ከሚለማው መሬት ከ10 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም