ተፈናቃዮች በሰፈሩባቸው አከባቢዎች የወረርሺኝ በሽታ እንዳይስፋፋ እየተሰራ ነው

76

አዲስ አበባ  መጋቢት 30/2011 ተፈናቃዮች በሰፈሩባቸው አከባቢዎች የወረርሺኝ በሽታዎች እንዳይስፋፉ የቅድመ መከላከል ሥራ እየተሰራ መሆኑን የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለጸ።

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በየነ ሞገስ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ ተፈናቃዮቹ ያሉበት ሁኔታ ምቹ ባለመሆኑ ለተለያዩ የወረርሺኝ በሽታዎች ተጋልጠዋል ብለዋል።

ለተቅማጥ፣ ለሆድ ጥገኛ ትላትል፣ ለመተንፈሸ አካላት ችግር፣ ቆዳ ላይ የሚከሰቱ በሽታዎች ለምሳሌ እከክ፣ ለምግብ እጥረትና ለሥነ-ልቦና ችግሮች መጋለጣቸውን ጠቁመዋል። 

ኢንስቲትዩቱም የተከቱት በሽታዎች ተዛማችነታቸውን ለመግታትና አዲስ ተገላጭነትን ለመቀነስ ተፈናቃዮቹ ባሉባቸው ሥፍራዎች ጊዜያዊ የጤና ተቋማት መቋቋማቸውን ገልጸዋል።

በዚህም ተፈናቃዮቹ የጤናና የጽዳት አገልግሎት እንዲያገኙ እንዲሁም የምግብ እጥረት ላሉባቸው የሥነ-ምግብ አገልግሎትና የምግብ እደላ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። 

በተለይም በጌዴኦ ዞን ለሚገኙ ተፈናቃይ ህጻናትና የሚያጠቡ እናቶች የደረሰባቸው የምግብ እጥረት ችግር ለማቃለል የምግብ እደላ ሥራው ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል። 

ጎን  ለጎንም የተለያዩ የሙያ ስብጥር ያላቸውን የጤና ባለሙያዎች በጊዜያዊ የእርዳታ ተንቀሳቃሽ ጤና ጣቢያዎቹ ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማስቻል  ሙያዊ ድጋፍ መደረጉንም ተናግረዋል።

እስካሁንም ከፌዴራል ተቋማት ብቻ ከ350 በላይ ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነው ሙያዊ እገዛ እንደተደረገላቸው መሆኑን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ኢንስቲትዩቱ የጤና አገልግሎት ሥራዎችን በተሳካ መልኩ ለማስኬድ የሚያስችል 480 ሚሊዮን ብር ለዚህ ጉዳይ ብቻ መድቦ ሥራ ላይ ማዋሉንም አስረድተዋል።

ያም ሆኖ አሁንም የመጸዳጃ ቤት እጥረት፣ የመጠለያ ቸግር፣ የጸጥታ ችግር፣ የክትባት እጥረትና የሰው ኃይል እጥረት የኢንስቲትዩትን ሥራ እያስተጓጎለው መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም