በዞኑ ሞዴል አርሶ አደሮች ምርጥ ተሞክሯቸውን እያካፈሉ ነው

102

ፍቼ/አምቦ መጋቢት 30/2011 በግብርናው መስክ ውጤታማ የሆኑ ሞዴል አርሶ አደሮች ምርጥ ተሞክሯቸውን ለሌሎች  እያካፈሉ መሆናቸውን በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ ።

በምዕራብ ሸዋ ዞን ደግሞ ለቀጣዩ መኸር የምርት ወቅት ዝግጀት እያደረጉ ነው

የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት  ምክትል ኃላፊ አቶ ፍቅሩ ከበደ  እንደገለፁት ተሞክሯቸውን እያካፈሉ ያሉት ጉልበት፣ መሬትና ውሃን  ተጠቅመው ከፍተኛ ገቢ ያገኙ  270 ሞዴል አርሶ አደሮች ናቸው ።

በዞኑ 13 ወረዳዎች የሚገኙት እነዚህ  ሞዴል አርሶ አደሮች ባለፉት ሶስት ዓመታት በግብርና ባለሙያዎች በመታገዝ አሰራራቸውን በማሻሻል፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ውጤታማ ሆነዋል፡፡

የሰብል የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የእንስሳት ምርታቸውን በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ ያገኙት ውጤት ለሌሎች አርሶ አደሮች እያካፈሉ መሆናቸውን  አቶ ፍቅሩ ተናግረዋል፡፡

በተለይ ምርጥ ዘር የተፈጥሮ ማዳበሪያ ከሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ጋር መጠቀምን ጨምሮ ሰብልን በመስመር  የመዝራት  ዘዴን ተግባራዊ በማድረግ  ያገኙት  ውጤት በየዘርፉ  ምርትን ያሳደገና ልምድ የሚቀሰምበት እንደሆነ  አስረድተዋል።

ከሞዴሎቹ መካከል በያያ ጉለሌ  ወረዳ የአቡ ይፋም  ቀበሌ አርሶ አደር ሙላቱ ሰርቤሳ  በሰጡት አስተያየት በበሬ ከማረስ ተነስተው በተያዘው ዓመት  ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር ህብረት በመፍጠር በገዙት የግል ትራክተር ማረስ  እንደጀመሩ ገልጸዋል፡፡

በዚህም ጊዜያቸውና ጉልበታቸውን በመቆጠብ  ምርታቸውን ማሳደግ እንደሚችሉ ከባለሙያ ተረድተው እየተጠቀሙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ላለፉት አራት ዓመታት የግብርና ባለሙያዎች ምክርና ድጋፍ በመጠቀም ካካሄዱት ልማት ከአንድ ሚሊዮን 500ሺህ ብር በላይ ግምት ያለው ንብረት ማፍራት እንደቻሉ ያስረዱት ሌላው አርሶ አደር ሙላቱ ሰርቤሳ    በከተማ   ቤት ሰርተው እየነገዱ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡

በወረዳው  የገጀብ አርሶ አደር በሃይሉ  አሰፋ  በበኩላቸው በሰብል ልማትና እንስሳት እርባታ ያገኙትን ምርጥ ተሞክሮ ተግባራዊ በማድረጋቸው በግላቸው ምርታቸውን ማሳደግ እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡

ገቢያቸውን ከመጨመር ባሻገር ለሌሎች አርሶ አደሮች ልምዳቸውን እያካፈሉ እንደሚገኙ አመልክተዋል።

"ከሞዴል አርሶ አደሮቹ ጥሩ የአስተራረስ ዘዴንና የግብአት አጠቃቀምን ልምድ ቀስሜያለሁ"  ያሉት በግራር ጃርሶ ወረዳ  የወርጡ ቀበሌ  አርሶ አደር አረዶ ሚለኬሳ  ናቸው፡፡

በተለይ በተያዘው ዓመትም በመስመር የመዝራት እና ተመሳሳይ የሰብል አይነቶችን በአንድ አካባቢ ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር በመስራት ዘዴ በመጠቀም ያገኙት  ተሞክሮ የእርሻ ስራቸውን እንዲያሻሽሉ እንደረዳቸው ተናግረዋል።

በዞኑ በ2010/2011 የምርት ወቅት እርሻ የተገኘውን 16 ሚሊዮን ኩንታል ምርት በቀጣዩ ዘመን በእጥፍ  ለማሳደግ ምርጥ ተሞክሮን ማስተዋወቅ ጨምሮ የግብዓትና የምርጥ ዘር አቅርቦት ከወዲሁ እየተሰራ መሆኑም ተመልክቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በምዕራብ ሸዋ ዞን በቀጣዩ መኸር የምርት ወቅት ከ614 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብል ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡

በዞኑ ግብርናና ገጠር ልማት ጽህፈት ቤት የሰብልና የአፈር ልማት ማሻሻያ ቡድን መሪ አቶ ባይሳ ተረፈ እንደተናገሩት በምርት ዘመኑ ለሚለማው መሬት ከ21ሚሊዮን ኩንታል ለማምረት ነው የታቀደው፡፡

በምዕራብ ሸዋ 22 ወረዳዎች ለሚገኙ ከ285ሺህ በላይ አርሶ አደሮች የሚያስፈልግ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ከወዲሁ በመቅረብ ላይ ይገኛል፡፡

እስካሁን ከ80 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ መቅረቡን አመልክተው ይህም ከታቀደው ከ60 በመቶ በላይ እንደሆነና ቀሪውም በፍጥነት ለማድረስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

ባለፈው ዓመት ያጋጠመው የበቆሎ ተምችና የስንዴ ዋግ በሽታ በድጋሚ እንዳይነሱ ቅድመ ጥንቃቄ እንዲደረግ ለአርሶ አደሩ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡

በደንዲ ወረዳ አርሶ አደር አበበ ተስፋዬ በሰጡት አስተያየት "ያለኝን ሁለት ሄክታር መሬት  በበቆሎ፣ ስንዴ፣ ጤፍ ለመዝራት ተዘጋጅቻለሁ" ብለዋል።

በምርት ዘመኑ  ከሚያለሙት  አንድ ሄክታር ተኩል መሬት ማደበሪያና ምርጥ ዘር ተጠቅመው ለማልማት እየተዘጋጁ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የግንደበረት ወረዳ አርሶአደር በሪሶ ቡልቶ ናቸው፡፡

የአምቦ ወረዳ አርሶአደር ሙሊሳ ጉተማ  በበኩላቸው በመጪው የመኸር ወቅት ባላቸው ሶስት ሄክታር በላይ መሬት ላይ በቆሎና  ሰሊጥ  ለማልማት የማሳ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

" ሰብሎቹን ሙሉ በሙሉ በመስመር ነው የምዘራው" ያሉት አርሶ አደሩ ሌሎች የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን ከሌሎች ገበሬዎች  ጋር ልምድ በመለዋወጥ ልማቱን እንደሚያከናውኑ ተናግረዋል፡፡

በምዕራብ ሸዋ ዞን በ2010/2011 የመኸር ወቅት ከለማው 615 ሺህ ሄክታር መሬት ከ17 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መሰብሰቡን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም