በተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያዎች የተከሰተውን የህጻናት የኩፍኝ በሽታ ለመከላከል ክትባት እየተሰጠ ነው

63

ጎንደር መጋቢት 30/2011 በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያዎች የተከሰተውን የህጻናት የኩፍኝ በሽታ ለመከላከል ክትባት በዘመቻ እየተሰጠ መሆኑን የዞኑ ጤና መምሪያ አስታወቀ፡፡

የመምሪያው ምክትል ኃላፊ አቶ ደስታው ክብረት ለኢዜአ እንደተናገሩት ክትባቱ እየተሰጠ ያለው በትክል ድንጋይ መጠለያ ውስጥ በአራት ህጻናትና ታዳጊዎች ላይ በሽታው በመታየቱ ነው፡፡

በሽታውን ለመከላከልም ከመጋቢት 27/2011 ዓ.ም. ጀምሮ በትክል ድንጋይ፣ አይምባና ጭልጋ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ለሚገኙ ዕድሜአቸው ከ6 ወር እስከ 15 ዓመት ለሆናቸው ህጻናትና ታዳጊዎች ክትባቱ እየተሰጠ ይገኛል፡፡

በጩሃይትና በጫንድባ መጠለያ ጣቢያዎችም በተመሳሳይ ክትባቱ መሰጠት ተጀምሯል፡፡

በዚሁ ለአንድ ሳምንት በሚቆየው የኩፍኝ መከላከያ ክትባት ከ7ሺ በላይ በመጠለያዎቹ ለሚገኙ ህጻናትና ታዳጊዎች ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡

በክትባት ዘመቻው በቂ የህክምና ባለሙያዎች ወደ መጠለያ ጣቢያዎቹ መላካቸውን የጠቆሙት ምክትል ኃላፊው የክትባት መድኃኒትም በተሟላ መንገድ መቅረቡን ገልጸዋል፡፡

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን 60ሺህ የሚጠጉ ተፈናቃዮች  በ11 ጊዚያዊ መጠለያዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተጠግተው እንደሚገኙ ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም