በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ አንድነት መገንባት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

70
ጅማ ግንቦት 25/2010 የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማጠናከር በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ አንድነት መገንባት አስፈላጊ መሆኑ ተገለጸ፡፡ ሁለተኛው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ኮንፈረንስ ዛሬ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል፡፡ የጅማ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ለሜሳ በኮንፈረንሱ ወቅት እንዳሉት የሀገር ዕጣ ፋንታ የሚወሰነው በውስጡ በሚኖሩ ህዝቦች መካከል በሚገነባው የአንድነት፣ የፍቅርና መተሳሰብን መሰረት የጋራ ተጠቃሚነት እሴት ላይ ነው፡፡ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፖለቲካ የእድገት ዘርፍ ጫፍ የደረሱ ሀገራት ልምድ እንደሚያሳየው በህዝቦቻቸው ልብ ውስጥ የታተመ ጠንካራ ሀገራዊ የአንድነት ስሜት አሁን ለደረሰበት የዕድገት ደረጃ መሰረት ሆኗቸዋል፡፡ "በነዚህ ሀገራት ውስጥ የኃይማኖት፣ የባህልና የቋንቋ ልዩነቶች ሳይኖር ቀርቶ ሳይሆን ከልዩነታቸው ይልቅ በአንድነታቸው ላይ በመስራታቸው በሰላምና በብልጽግና ህይወት ይኖራሉ" ብለዋል ፕሮፌሰር ፍቅሬ፡፡ ወደተሻለ የብልጽግና ማማ ለማውጣት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ አንድነት መገንባትና ማጠናከር እንደሚያስፈለግ ገልጸዋል፡፡ በኮንፍረንሱ ከተሳተፉት መካከል የጅማ አካባቢ የሀገር ሽማግሌ የሆኑት አቶ አብዱልከሪም አባገሮ በበኩላቸው የአማራ፣የኦሮሞና የሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦችን አንድነት ከጥንት ጀምሮ በንግድ፣ በኃይማኖት፣ በጋብቻና በሌሎችም ማህበራዊ ጉዳዮች የነበረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ "አሁን መሰራት ያለበት ጉዳይ አንድነትን የማጠናከር ስራን ማሰቀጠል ነው" ብለዋል፡፡ ሌላው የኮንፍረንሱ ተሳታፊ ረዳት ፕሮፌሰር ከተቦ አብዮ በበኩላቸው የአማራና ኦሮሞ ከጥንት ጀምሮ አብረው በሰላም የኖሩ ህዝቦች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ እንደ ደቦ፣ የአይናባት፣ እቁብና የመሳሰሉ ማህበራዊ ግንኙነቶች ህዝቦች በአንድነትና በሰላም አብሮ እንዲኖሩ እገዛ ማድረጋቸውን አመልክተዋል፡፡ በህዝብ ለህዝብ ኮንፈረንሱ በኦሮሞና በአማራ ሕዝብ መካከል ያለው ታሪክ እና ባህላዊ ባህሪ እንዲሁም አንድነት ላይ የወለጋና የደብረማቆስ ዩኒቨርስቲዎች ያካሄዱትና ሌሎችም ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደረጎባቸዋል፡፡ በኮንፍረንሱ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ዶከተር ነገሪ ሌንጮ ፣ አርቲስት አሊ ቢራ፣ ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የተወጣጡ ምሁራንና የተማሪዎች ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡ የመጀመሪያው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ኮንፍረንስ ባለፈው ዓመት በደብረብረሃን ዩኒቨርሲቲ መካሄዱ  ይታወቃል፡፡        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም