ሀገራዊ ለውጡን ከዳር ለማድረስ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ተባለ

62

አርባምንጭ መጋቢት 30/2011 በሀገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ ከዳር ለማድረስ በሚደረገው ጥረት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸው ተገለጸ።

የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዴፓ) 29ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተከብሯል፡፡

" መደማመጥ ለቀጣይ የስኬት ጉዞ " በሚል መሪ  ቃል ትናንት በዩኒቨርሲቲው በተከበረው በዓል ላይ በተቋሙ የኦዴፓ አስተባባሪ አቶ አብደላ ቲቤሶ እንደገለጹት ሀገራዊ ለውጡ ከዳር እንዲደርስ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል።

በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ተሳትፎ የመጣው ሀገራዊ ለውጥ እንዳይቀለበስ ሁሉም አካል አካባቢውን በንቃት ሊጠበቅና ከለውጡ ጎን ሊሰለፍ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራ ለማደናቀፍ  የሚፈልጉ አካላት የሀሰት መረጃ ሲያሰራጩ መቆየታቸውንም አስታውሰዋል።

"ተማሪዎች  የብሔር ግጭት ውስጥ እንዲገቡ በርካታ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል" ያሉት አቶ አብደላ በጋሞ ባይራ ሽማግሌዎች ጥረትና በተማሪዎች ምክንያታዊ አስተሳሰብ የጥፋት ኃይሎች ሙከራ አለመሳካቱን አስረድተዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የመጡ ተማሪዎችን የያዘ የኢትዮጵያ ተምሳሌት በመሆኑ ተማሪዎች የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ ከዳር ለማድረስ እርስ በርስ መቻቻልና መተባበር እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር የቻለ ከበደ በበኩላቸው ለውጡን ተከትሎ ህብረተሰቡን የሚከፋፍሉና አንድነቱን የሚሸረሽሩ አስተሳሰቦች በስፋት እየተስተዋሉ መምጣታቸውን ገልጸዋል።

"የሀሳብ ብዝሃነትን ማስተናገድ አማራጭ የሌውም ጉዳይ ነው" ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ሕብረተሰቡ በተለይ ወጣቱ በእኩይ አጀንዳ ከመጠመድ ይልቅ ድህነትን ለማሸነፍ ጠንክሮ መስራት እንዳለበት አመልክተዋል።

በእውቀት፣ በክህሎት፣ በአመለካከትና በስነ-ምግባር የዳበረ ብቁ የሰው ኃይል ማፍራት የሚቻለው ሰላም ሲኖር በመሆኑ ተማሪዎችና የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የሰላም አምባሳደር መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል ፡፡

ባለፉት 29 ዓመታት በነበረው የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የኦዴፓ አስተዋጽኦ የጎላ እንደነበር የገለጹት ደግሞ በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የኦዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ኤፍሬም ተሰማ ናቸው።

የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ ወቅቱ በሚጠይቀው ፍጥነት ልክ ከመምራት ጋር በተያያዘ ችግሮች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

"በአሁኑ ጊዜ እኔ አውቅልሃለሁ የሚለው አስተሳሰብ ተቀርፎ በውይይትና በሀሳብ ልዕልና የሚመራ የፖለቲካ ምህዳር ተፈጥሯል" ያሉት ተወካዩ  የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ ለማስቀጠል ኦዴፓ ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠንክሮ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ኮሌጅ የ2ኛ ዓመት ተማሪ የሆነችው ኢማን ማህመድ " የጋራ ሀገራችንን ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ መደማመጥ ባህላችን ሊሆን  ይገባል" ብላለች።

በሃይድሮሊክስ ምህንድስና የ5ኛ ዓመት ተማሪው ሙላለም እንዳሻው በበኩሉ እየተስተዋሉ ያሉት የዜጎች መፈናቀልና በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚለቀቁ የሀሰት መረጃዎች ለሀገሪቱ ፈተና መሆናቸውን አመልክቷል።

የህግ ማዕቀፍ በማዘጋጀት ጭምር ችግሩን ለመቅረፍ መንግስት ጥረት እያደረገ መሆኑን የጠቆመው ተማሪ ሙላለም ለጥረቱ ስኬታማነት የበኩሉን እንደሚወጣ ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም