የገቢዎች አገልግሎት አሰጣጥ መሻሻሉና የኮንትሮባንድ ንግድ መቀነሱ ነጋዴውን ያበረታታል - የንግዱ ማህበረሰብ

91

መጋቢት 29/2011 በገቢዎች ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶች  መሻሻሉና የኮንትሮባንድ  ንግድ እየቀነሰ መምጣቱ ህጋዊ ነጋዴውን የሚያበረታታ መሆኑን  አስተያየታቸውን የሰጡ ነጋዴዎች ተናገሩ፡፡

በገቢዎች ሚኒስቴር የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የአዲስ አበባ አንዳንድ ነጋዴዎች አስተያየታቸውን ለኢዜአ ሰጥተዋል ፡፡

በልብስ ንግድ ስራ ላይ  የተሰማሩት አቶ አብረሃም ሀይሌ  በሰጡት አስተያየት ˝ነጋዴው ከግብር  ጋር የሚያጋጥሙትን ቅሬታዎች ለማቅረብ በተለያዩ ቦታዎች እንዲሄድ እና ለብዙ ቀናት የሚንገላታበት  አካሄድ ቀርቶ በአንድ ቦታና በፍጥነት መልስ የሚሰጥበት ሁኔታ ትልቅ መሻሻል አለው˝ ነው ያሉት ፡፡

ከዚህ በፊት ወደ መርካቶ በስፋት ሲገባ የነበረው የኮንትሮባንድ እቃ መቀነሱ ለህጋዊ ነጋዴው ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ መሆኑንም አቶ አብረሃም ተናግረዋል፡፡

ደረሰኝ የማይቆርጡ ነጋዴዎችን ለመቆጣጠር የሚደረገው ክትትልም እየተጠናከረ መምጣቱን የገለጹ አቶ አብረሃም፤ ጅምላ አከፋፋይ ነጋዴዎች ላይ ከደረሰኝ አለመቁረጥ ጋር ተያይዞ የሚስተዋለው  ችግር  በቸርቻሪው ነጋዴ ላይ ተጽዕኖ እየፈጠረ በመሆኑ ቁጥጥሩ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡

በጥቃቅንና አነስተኛ በተደራጁ ግለሰቦች የተመረቱ ምርቶችን  ለማበረታታት በመንገድ ዳር የሚዘጋጁ ባዛሮች አላማቸውን ሲስቱና ከሱቅ ነጋዴው ጋር ተመሳሳይ ምርት የሚሸጡበት ሁኔታ የሱቅ ኪራይና  ግብር ከፍሎ የሚሰራውን ነጋዴ ገባያ የሚያሳጡበት ሁኔታ መኖሩንም ነው አቶ አብረሃም የጠቆሙት፡፡

የገቢዎች ሚኒስቴር ደረሰኝ የማይቆርጡ ጅምላ አከፋፋዮች ላይ የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ የጀመረው ስራ ለረጅም ጊዜ በነጋዴው ሲነሳ የነበረውን ቅሬታ እየፈታ መሆኑን የተናገሩት የተለያዩ የመዋቢያ ቅባቶችን አምርቶ ለገበያ በማቅረብ ስራ ላይ የተሰማሩት አቶ አሸናፊ አረጋ ናቸው፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አገልግሎት  አሰጣጡን ምቹ ለማድርግ  የጀመረውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ በመቀጠል ያለአግባብ ዋጋ በሚጨምሩት ላይም ክትትል ሊያደርግ ይገባዋል ነው ያሉት፡፡

በገቢዎች በኩል ‘’መብራት ጠፋ ሲስተም የለም’’ በሚል አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ የቆዩ ችግሮች  አሁንም ችግር ሆነው መቀጠላቸውን የሚገልጹት በመርካቶ የልብስ ንግድ ስራ ላይ የተሰማሩት አቶ ፉአድ ሀሰን  ናቸው፡፡

˝ወርሃዊ ሂሳብን ለማሳወቅ ወደ ገቢዎች ቅርንጫፍ ስንሄድ ሲስተም የለም በሚል በ10 ደቂቃ የሚያልቅ ስራ ቀኑን ሙሉ የሚያውልበት ሂደት አለ˝ ብለዋል፡፡

የገቢዎች  ሚንስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው  የንግዱ ማህበረሰብ በተቋሙ ላይ ስለ አገልግሎት አሰጣጥና ፍትሃዊነት የሚያነሳውን ጥያቄዎች በዘላቂነት ለመመለስ  ተቋሙን እንደገና የማደራጀት፣ የተንዛዙ አሰራሮችን የማስተካከልና  የኮንትሮባንድ ንግድን በመቆጣጠር በኩል በተሰሩ ተግባራት  ውጤት እየተገኘበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በሀገሪቱ አንዱ ነጋዴ  ግብር የሚከፍልበት፤ ሌላው ሳይከፍል እንደፈለገ የሚሆንብት አሰራር እንዲስተካከል  በመደረጉ፤  ነጋዴው ሲያነሳው የነበረው የፍትሃዊነት ችግር መቀረፉንም ሚኒስትሯ አስረድተዋል፡፡

በስፋት ሲገባ የነበረውን የኮንትሮባንድ ሸቀጥ ለመቆጣጠር በሀገሪቱ የነበሩ 55 የመቆጣጠሪያ ኬላዎችን ወደ 94 በማሳደግ፣ በተማረ የሰው ሃይል በማደራጀትና የቁጥጥር ስራን በማጠናከር ችግሩ እየቀነሰ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትሯ እንዳሉት ባለፈው አንድ አመት ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮብ ብር በላይ የሚያወጣ የኮንትሮባንድ  እቃ መያዙንና ቁጥጥሩን ለማጠናከር  600 የጉምሩክ ፖሊሶች እንዲመደቡ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

ለንግዱ ማህበረሰብ በሚሰጡ አገልግሎቶች ላይ ሲስተዋሉ የነበሩትን አላስፈላጊ መጉላላት  ለመቀነስ በተቋሙ የነበሩ ረጂም ሰንሰለት በማስቀረት አገልግሎቶች በአንድ ማእከል  እንዲያልቁ መደረጋቸውንም ነው ሚኒስትሯ ያስረዱት፡፡

ተቋሙ ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ግንኙነት በማሳደግ ከመብራትና ከኢንተርኔት ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮችን  ለመቅረፍ  በጋራ እየተሰራ እንደሚገኝና የተቋሙን አገልግሎት አሰጣጥን በቴክኖሎጂ በማዘመን ተገልጋዩ ባለበት ሆኖ እንዲስተናገድ የሚያስችል የህግ ማእቀፍ እየተዘጋጀ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም