በሀገሪቱ የሚገኙ የተሽከርካሪ ማቆሚያዎች አብዛኞቹ ደረጃቸውን ያልጠበቁ ናቸው ተባለ

90

መጋቢት 29/2011 በሀገሪቱ የሚገኙ የተሸከርካሪ ማቆሚያ ስፍራዎች አነስተኛ ከመሆናቸው በተጨማሪ  አብዛኞቹ ዝቅተኛ የሚባለውን ደረጃ ያላሟሉ መሆናቸውን የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ገልጿል፡፡

የባለስልጣኑ የከተማና ገጠር ትራንስፖርት አገልግሎት ድጋፍና ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ባዩ ሙሉጌታ እንደተናገሩት የንግድ ማዕከላት፣ ሆቴሎችና ሌሎች ተቋማት ለደንበኞቻቸው ያዘጋጁት ማቆሚያ ቦታዎች ካልሆኑ በስተቀር በሀገሪቱ ያሉት የተሽከርካሪ ማቆሚያ ስፍራዎች ጥቂትና ደረጃቸውን ያልጠበቁ ናቸው፡፡

በመሆኑም በአገሪቱ  ከተሞች ለህዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ተሸከርካሪዎችን ጨምሮ ሌሎች ተሽከርካሪዎች በመንገድ ዳር በመቆም የትራፊክ መጨናነቅ በመፍጠር ለአደጋ የሚያጋልጡና ለመንገዶች መበላሸት  ምከንያት እየሆኑ ነው ብለዋል፡፡

ለመንገድ ግንባታው እንጂ ለተሽከርካሪ ማቆሚያ ትኩረት ባለመሰጠቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ በከተሞች የማቆሚያ ስፍራ አለመስፋፋትና አለመዘመን ምክንያት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

የትራንስፖርት ፖሊሲ አለመቀረጹ ለመኪና ማቆሚያ ስፍራዎች አለመስፋፋትና ባለሃብቶች በመኪና ማቆሚያ ስፍራ የሚሳተፉበት መመሪያ አለመውጣቱ አንዱ ችግር እንደሆነ ነው አቶ ባዩ  የገለጹት፡፡

አብዛኞቹ ከተሞች በማስተር ፕላናቸው ውስጥ የማቆሚያ  ቦታ አለማካተታቸውን ያመለከቱት ዳሬይሬክተሩ  በአዲስ አበባ በማስተር ፕላን ተካቶ፤  ቦታዎቹ ተለይተው ዘመናዊ ማቆሚያ ስፍራ መገንባት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም በአገር አቀፍ ደረጃ የሚታየውን የማቆሚያ ችግርን ለመፍታትና ደረጃቸውን የጠበቁ የማቆሚያ ሥፍራዎችን ለመገንባት የሚያስችሉ የትራንስፖርት ፖሊሲ ማዘጋጀትና ሌሎች ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የትራንስፖርት ፖሊሲው ተዘጋጅቶ ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት መላኩን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤  ባለሃብቶች በማቆሚያ ስፍራው ግንባታ የሚሳተፉበት መመሪያ መዘጋጀቱንም አብራርተዋል፡፡

በሀገሪቱ ዘመናዊ የተሸከርካሪ ማቆሚያ ስፍራዎችን ለመገንባት በአሁኑ ወቅት የዲዛይን ስራና ሌሎች ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ የህዝብ ግኑኝነት ዳሬክቶሬት ዳሬክተር አቶ  ታመነ በሌ በበኩላቸው በከተማ አስተዳደሩ መሪ ፕላን ስልሳ  ቦታዎች ለተሸከርካሪ ማቆሚያ ስፍራ ተለይተው ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ የግንባታ ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡  

ከተማዋ  እስከ ቅርብ ግዜ ድረስ ደረጃውን የጠበቀ  የተሸከርካሪ ማቆሚያ እንዳልነበራት የጠቀሱት አቶ ታመነ፤ ማስተር ፕላኑ መውጣቱን ተከትሎ  በመገናኛ፣  ወሎ ሰፈርና መርካቶ አካባቢ ደረጃቸውን የጠበቁ  ማቆሚያ ስፍራ መገንባቱን  ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ በጀት ዓመትም በማስተር ፕላኑ በተለዩ ቦታዎች ላይ አምስት የማቆሚያ ስፍራዎች  እንደሚገነባ የተናገሩት ዳይሬክተሩ በዚህ አመት አስራ ሶስት የሚሆኑ ለልማት ሳይውሉ የቆዩ ቦታዎችን በግዜያዊነት ለተሸከርካሪ ማቆሚያ እንዲውሉ ተደርጓል ብለዋል ፡፡

ለህዝብ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሸከርካሪዎች ተሳፋሪን የሚያሳፍሩበትና የሚያወርዱበት ቦታ ቅድሚያ ተሰጥቶት ሥራው  መጀሩንም ጨምረው ገልጸዋ ፡፡

እንደ ዳሬክተሩ ገለጻ በአዲስ አበባ የሚገኙ የማቆሚያ ስፍራዎች  ለህዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ተሸከርካሪዎችን  ጨምሮ ለማንኛውም ተሸከርካሪዎች አገልግሎት የሚሰጡ ቢሆንም   በማቆሚያ ቦታዎች  ያለማቆም ችግር ይስተዋላል ብለዋል፡፡

በዘረፉ ያሉት ችግሮች በርካታ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ታመነ፤ ለመፍትሔውም የሚመለከታቸው አካላት ርብርብን እንደሚጠይቅ ተናግረዋል፡፡  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም