ጤናቸው በጤና ማዕቀፎች ትግበራ መጠበቁን የምዕራብ አዘርነት በርበሬ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ

73

ሆሳዕና  መጋቢት 29/2011 ጤናቸው የጤና ማዕቀፎችን በመተግበር እንደተጠበቀላቸው በስልጤ ዞን የምዕራብ አዘርነት በርበሬ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

በጤና ሚኒስቴር የተዘጋጀና በወረዳ ትራንስፎርሜሽን በተከናወኑ ሥራዎች ላይ ያተኮረ የልምምድ ልውውጥና ጉብኝት በወረዳው ተካሂዷል፡፡

ሞዴል የቤተሰብ አባላት፣ትምህርት ቤቶች፣የጤና ድርጅቶች የጉብኝቱ አካል ነበሩ፡፡

በወረዳዉ ምዕራብ ሙጎ ቀበሌ ዥሌ ገመሶ ጎጥ ሞዴል ቤተሰብ እማወራ ወይዘሮ መርዲያ ሼህ አብዱልመና በማዕቀፉ በተሰጣቸው ስልጠና ተጠቃሚ ሆኛለሁ ከሚሉት መካከል ናቸው፡፡

በማዕቀፉ ከመካተታቸው በፊት እናቶች በቅድመ ወሊድና ድህረ ወሊድ ሂደት ላይ ክትትል ለህልፈት እንደተዳረጉ ያስታውሳሉ፡፡

የግልም ሆነ የቤተሰባቸውን ብሎም የአካባቢያቸውን ጽዳት ባለመጠበቃቸው ለሕመም ይዳረጉ እንደነበርም ያወሳሉ፡፡

አሁን ግን በማዕቀፍ ተደራጅተው ከነቤተሰባቸው የማህበረሰብ ጤና መድህን አባል በመሆን በፈለጉት ጊዜ ሕክምና እንደሚያገኙ ገልጸዋል፡፡

የዚሁ ቀበሌ ነዋሪው አቶ  አብዱራህማን ያሲን ጽዳትን ከራስና ከቤት በመጀመራቸው የጤና ችግሮች መከላከል ችያለሁ ይላሉ።

ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ በሕመም ሲጠቁና ሕክምና ሲከታተሉ እንደኖሩ የሚገልጹት ሌላኛዋ የቀበሌዋ ሞዴል እማወራ ወይዘሮ ሙሪዳ አርጋ፣

የሕክምና ወጪያቸው ከገቢያቸው ጋር ባለመመጣጠኑ ይጎዱ እንደነበር ያስረዳሉ።

በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አገልግሎት ሕይወታቸውን እንደታደጋቸውን ወጪያቸውን እንደቀነሰላቸው ተናግረዋል፡፡

የስልጤ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ አብድልዋሪስ ጀማል እንደገለጹት በዞኑ 132 ሺህ እማወራና አባወራዎች የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አባል ናቸው፡፡

ይህም የአባልነት ምጣኔው 81 ከመቶ አድርሶታል ብለዋል፡፡

በጤና ተቋም የሚሰጠዉን የወሊድ አገልግሎት ሽፋን ለማሳደግ፣ የእናቶች ማቆያ ማስገንባትና የወሊድ ጊዜያቸው የደረሰባቸው እናቶች በማቆየት አገልግሎት ማግኘታቸውንም አስረድተዋል፡፡

በቤተሰብና በማህበረሰብ ደረጃ የጤና ኤክስቴንሽን መርሐ ግብር በመተግበር በ29 ቀበሌዎች 95ሺ 988 ሞዴል  ቤተሰቦች መሳተፋቸውን ገልጸዋል፡፡

የጤና  ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አስቻለው አባይነህ እንደገለጹት ባለፉት አራት ዓመታት በአገር አቀፍ ደረጃ በጤናው ዘርፍ  አንድ ሺህ ወረዳዎች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

በዘርፉ ውጤታማ ከሆኑት ስምንት ወረዳዎች አንዱ የስልጤ ዞን ምዕራብ አዘርነት በርበሬ ወረዳ እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡

''ወረዳው ሞዴል የሆነው ከኅብረተሰቡ ጋር በቅንጅት በመስራቱ ነው'' ያሉት አቶ አስቻለው፣የወረዳውን ተሞክሮ በሌሎች ወረዳዎች ለማስተዋወቅ ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡

ሕዝበ ውጤቱን በማስቀጠል ርብርብ እንዲያደርግ ኃላፊው ጠይቀዋል፡፡

በጉብኝቱ የፌዴራል፣ የደቡብ ክልልና የዞን ባለስልጣናትና የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም