መንግስት ምጣኔ ኃብታዊ የመዋቅር ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ጠንካራ መሰረት እየጣለ ነው - የዘርፉ ባለሙያዎች

50

አዲስ አበባ  መጋቢት 29/2011 የኢትዮጵያ መንግስት የአገሪቱን ምጣኔ ኃብታዊ የመዋቅር ለውጥ ሂደት እውን ለማድረግ የሚያስችል ጠንካራ መሰረት እየጣለ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ገለፁ።

ኢትዮጵያዊ ዜና አገልግሎት ያነጋገራቸው ባለሙያዎቹ የዛሬ ዓመት የተጀመረው ሁለንተናዊ አገራዊ የለውጥ ሂደት ግብ ዘላቂ የምጣኔ ኃብት እድገትን ለማምጣት የሚያስችል መሰረት መጣል መሆኑን ጠቅሰዋል። 

እንዲያም ሆኖ ይህንን የምጣኔ ኃብታዊ ለውጥ ለማሳካት የግሉን ክፍለ ኢኮኖሚ በስፋት ለማሳተፍ የተጀመረው ጥረት ውጤታማ በሆነ መንገድ እውን እንዲሆን ሂደቱን በብቃት መከታተል የሚችሉ  ተቋማት ያስፈልጋሉ ሲሉም አሳስበዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፖሊሲ ጉዳዮች አማካሪ የነበሩት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸ እንደሚሉት በአገሪቱ ምጣኔ ኃብታዊ የመዋቅር ለውጥ ለማምጣትና የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማጠናከር በመንግስት እየተከናወነ ያለው ተግባር ዘላቂ እድገትን ለማስመዝገብ የሚያስችል፣ ወቅታዊና የሚደነቅ ነው።

በተለይም የመንግስት ይዞታ የሆኑ ትላልቅ የኢኮኖሚ አውታሮችን ወደግል በማዘዋወር የግሉን ዘርፍ የምጣኔ ኃብታዊ እንቅስቃሴ ለማጠናከር እየተወሰደ ያለው እርምጃ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሚስተዋለውን ሥራ አጥነት ለማቃለል ብሎም አገራዊ ኃብት ለመገንባት ዓይነተኛው ስልት ነው ሲሉም አክለዋል።

“ኢትዮጵያዊ ውስጥ በግሉ ዘርፍ በኩል እጅግ ከፍተኛ የሆነ እድሎች አሉ፤ በተለይም  ቴሌኮሙኒኬሽንን፣ የባቡር ትራንስፖርትን፣ የባህር ትራንፖርትንና ሎጂስቲክ አገልግሎቶችን አንደዚሁም የኃይል አቅርቦትንና በመሳሰሉት የአገሪቱ ዋነኛ የሚባሉ የኢኮኖሚ አውታሮች የግሉ ዘርፍ የሚሳተፍበትን ሁኔታ ለማመቻቸት መወሰኑ መንግስት ከፍተኛ የመዋአለነዋይና የፋይናንስ ኃብት ለማፍራት ያግዘዋል።”  በማለት አመልክተዋል።

በግብርና ልማት ላይ የተመሰረተውን የኢትዮጵያ የምጣኔ ኃብታዊ መሰረት ወደአግሮ ኢንዱስትሪ በማሻገር በዘርፉ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት መንግስት የጀመረው ጥረት አገራዊ የብድር አቅምን እና የመዋእለ ንዋይ ገበያን ለማጠናከር የሚያስችል መሆኑንም ዶክተር ቆንስጣነጢኖስ ተናግረዋል።

የግሉ ዘርፍ የፋይናንስ አቅምን ለማሳደግ፣ የሥራ እድልና የተነቃቃ ገበያ ለመፍጠር ቁልፍ መሳሪያ መሆኑን የጠቀሱት ባለሙያው ሆኖም ዘርፉ በአገሪቱ ምጣኔ ኃብት መስተጋብር ውስጥ ሊጫወት ሚገባውን ሚና ውጤታማ ለማድረግ ጠንካራ ተቋማትና በቂ የፋይናንስ አቅርቦት ሊኖር ይገባል ብለዋል። 

የግሉ ዘርፍ ማነቆ ናቸው የሚባለው የፋይናንስ አቅርቦትን ማሻሻል ይቻል ዘንድም የአገሪቱን የባንክ አሰራር ስርዓት መለወጥ እንደሚገባም አሳስበዋል።

በተለይም ከአገር አልፎ በዓለም አቀፍ ትላልቅ ኩባንያዎች ጭምር ከፍተኛ ፍላጎት እያሳደረ ያለውንና  የመንግስት ይዞታን ወደግል ለማዘዋወር የተቀየሰው ስልት ውጤታማ ለማድረግ የእነዚህ ተቆጣጣሪ ተቋማት መኖር ወሳሽ እንደሆነም አንስተዋል።

በአፍሪካ ልማት ባንክ ዋና የምጣኔ ኃብት ባለሙያ የሆኑት ኤድዋረድ ቢ ሴኖኛ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት የመንግስት ከፍተኛ ተሳትፎ የሚስተዋልበት የኢትዮጵያ ምጣኔ ኃብት እድገት የተለያዩ ውስንነቶች ያሉበት መሆኑን ጠቅሰው እነዚህ ውስንነቶች በግሉ ዘርፍ ተሳተፎ ሊጠናከሩ እንደሚችሉ አስረድተዋል።

በመሆኑም መንግስት የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማጎልበት በሚል በቅርቡ ያሳለፈው ውሳኔ  ጠቃሚና የሚደነቅ ነው ብለዋል። መንግስት የጀመረው የምጣኔ ኃብት ግንባታ በዘላቂነት የሚሳካው በጠንካራ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ መሆኑንም አብራርተዋል።

የመንግስት ይዞታ የሆኑ የምጣኔ ኃብት አውታሮችን ወደግል ለማዞር የተጀመረው እንቅስቃሴ ፍሬያማ እንዲሆን ጠንካራ ተቋማት ሊኖሩ ግድ ይላል፤ በዚህ ረገድ የተጀመረውን ለውጥ በአግባቡ መምራት እንዲቻልም የሌሎች አገራት መልካም ተመክሮን ማጤን ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም