በመቀሌ ሲካሄድ የሰነበተው ሀገር አቀፉ የትምህርት ቤቶች ስፖርት ውድድር ተጠናቀቀ

77

መቀሌ መጋቢት 29/2011 በመቀሌ ከተማ  ሲካሄድ የሰነበተው ሶስተኛው ሀገር አቀፍ  የትምህርት ቤቶች ስፖርት ውድድር ትናንት ማምሻውን በደማቅ ስነስርዓት ተጠናቀቀ።

በ20 የስፖርት ዓይነቶች በተካሄዱት ውድድሮች ኦሮሚያ 96 ወርቅ፣ 81 ብርና 61 ነሐስ በማግኘት አንደኛ ሲወጣ አማራ ደግሞ ወርቅ 79፣ ብር 75 እና 74 ነሐስ ሜዳሊያ ይዞ ሁለተኛ ወጥቷል፡፡

ትግራይ ደግሞ 57 ወርቅ፣ 67 ብርና 65 ነሐስ በማግኘት ሶስተኛ ሲወጣ አዲስ አበባ አስተዳደር 25 ወርቅ ፣ 23 ብርና 51 ነሐስ በማግኘት ቀጣዩን ደረጃ ይዞ አጠናቋል፡፡

በመዝጊያው ስነስርዓት ወቅት የትምህርት ሚኒስተር ዴኤታ አቶ መሃመድ አህመዲን "ሀገር አቀፉ የትምህርት ቤቶች ስፖርት ውድድር ህብረብሔራዊነት የተረጋገጠበት ነው " ብለዋል።

በመቀሌ የታየውን  ፍቅርና አንድነት ዘላቂነት እንዲኖረው ሊሰራ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን  ምክትል ኮሚሽነር ጌታቸው ባልቻ በበኩላቸው በመቀሌ የተካሄደው የስፖርት ውድድር ተተኪዎችን ለማፍራት የሚያግዝ መሰረት ያጣለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳደር ማዕርግ የከተማ ልማት፣ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አብርሃም ተከስተ በበኩላቸው ውድድሩ በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላደረጉ ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የመቀሌ ከተማና አካባቢው  ነዋሪዎች  ከተለያዩ ክልሎች ለመጡ ስፖርተኞች እንደቤታቸው ተቀብለው በማስተናገድ ለሰጡት ድጋፍም አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡

እያንዳንዱ ወጣት ስፖርተኛም በየአከባቢው የሰላምና የፍቅር አምባሳደር እንዲሆንም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ከተለያየ ክልል ለመጡ 3ሺህ 500 ስፖርተኞች ፣ አሰልጣኞችና አመራሮች በሰላም እንደመጡ በሰላም ወደየቤታቸው እንዲመለሱ መልካም ምኞታቸውን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ገነት አረፈ ናቸው።

ከኦሮሚያ ክልል የመጣው ወጣት ሎግያ አዱኛ የመቀሌ  ህዝብ መልካም መስተንግዶ በቆይታው እንደተመቸው ተናግሯል፡፡

" በመቀሌ ከተማ የሚገኝ ህዝብ ከየቀበሌው የሚጠጣ ንጹህ ውሃና፣ምግብ ወደ ስፖርተኞች ይዞ በመምጣት ያለውን ፍቅር በተግባር አሳይቶናል" ያለው ደግሞ ከደቡብ ክልል የመጣው  ወጣት ቴዎድሮስ ሃብታሙ ነው፡፡

ህዝቡ ያሳያቸውን  ጥልቅ ፍቅርና መስተንግዶ ወደየ ትምህርት ቤቶቻቸው ሲመለሱ  የሰላም አምባሳደር በመሆን ለመስራት ጥረት እንደሚያደረግ ተናግሯል፡፡

ከአማራ ክልል የመጣችው ወጣት ወይንሸት መልአኩ በበኩሏ ውድድሩ በሀገሪቱ  የሚታየውን የመለያየት ስሜት በማስተካከል  ፍቅርን ለማጎልበት እንደሚያግዝ ገልጻለች፡፡

" ሁሌም እንዲህ ዓይነት መድረክና አጋጣሚ ቢፈጠር ለአንድነታችን መልካም አጋጣሚ ነው" ብላለች፡፡

ከመጋቢት 14 እስከ መጋቢት 28 ቀን 2011 ዓ.ም.   ሲካሄድ የቆየው ሀገር አቀፉ የትምህርት ቤቶች ስፖርት  ውድድር ትናንት ማምሻውን በደማቅ ስነ ስርዓት ሲጠናቀቅ  በሺዎች የሚገመቱ የመቀሌና አካበባቢው ነዋሪዎች  በተገኙበት የተለያዩ ባህላዊ ዝግጅቶች ቀርበዋል።

የትግራይ ክልል ከሁለት ዓመታት በኋላ ለሚካሄደው  የትምህርት ቤቶች ስፖርት ውድድርን ለሚያዘጋጀው የኦሮሚያ ክልል አስረክቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም