የአውሮፓ ህብረት ለሩዋንዳ ያለውን አጋርነት ገልጿል

57

መጋቢት 29/2011 የአውሮፓ ህብረት ሩዋንዳ አክብራ የምትውለውን 25 ተኛ አመት የዘር ማጥፋት መታሰቢያ በማስመልከት ለሃገሪቱ ያለውን አጋርነት ገልጿል፡፡

ሲጂቲኤን አፍሪካ እንደዘገበው በአሰቃቂው የሩዋንዳ የዘር ማጥፋት 1 ሚሊየን ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል፣በበሚሊየኖች የሚቆጠሩም ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል፣ለብዙ ቤተሰቦች መለያየት ምክንያት ሆኗል ፡፡

ከሚያዚያ እስክ ሃምሌ ለ100 ቀናት የተፈፀመው ይህ የዘር ማጥፋት ድርጊት ብዙዎችን ከሃገራቸው  እንደወጡ እንዳይመለሱም አድርጓል፡፡

ህብረቱ ትናንት ባወጣው መግለጫ ሃገሪቱ ይህ ድርጊት ከተፈፀመ በኋላ ላሳየችው እድገት አድናቆቱን ቸሯቷል ፤ አለም አቀፉ ማህበረሰብም ሃገሪቱን መደገፉን እንዲቀጥል ጠይቋል፡፡

“ሩዋንዳ ከ25 አመት በኋላ በብዙ መልኩ የተቀየረች ሃገር ሆናለች ይህም ህዝቦቿ የራሳቸውን ህይወትና ሃገራቸውን ለመገንባት ባሳዩት ቁርጠኝነት ነው ለዚህም ምስጋና ይገባቸዋል ፤ብሄራዊ መግበባትንም እውን አድርገዋል፤ለዚህም ጥረታቸው አለም አቀፉ ማህበረሰብ አጋርነቱንና ድጋፉን ሊያሳያቸው ይገባል”ብሏል መግለጫው፡፡

“የመታሰቢያው ስነስርአት ካለፈው ለመማር እድል ይሰጣል ፤ከዚህም ቀጣናውና አለምም ሊማርበት ይገባል፣በአሁኑ ሰአት አለም አቀፍ እሴትን በመጋራት ተጠያቂነትን በማረጋገጥና የሃገራት ትብብር ከምንጊዜውም በላይ የሚያስፈልግበት ነው”ሲልም አክሏል፡፡

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ጨምሮ ሩብ ምእተ አመትን ባስቆጠረው የዘር ማጥፋት መታሰቢያ ላይ ለመታደም የኮንኮው ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ዴኒስሳሶ ኒጌሶ ፣የኒጀር ፕሬዝዳንት ማሃማዶ ኢሶፉ ፣የጅቡቲው ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሊይና የቤልጂየም ጠቅላይ ሚኒስትር ቻርለስ ሚቼል እና ሌሎችም መሪዎች ተገኝተዋል፡፡

ከሚካሄዱ የመታሰቢያ ስነስርአቶች መካከል መሪዎቹ 250 ሺህ ሰዎች በጋራ በተቀበሩበት የኪጋሊ የዘር ማጥፋት መታሰቢያ  ስፍራ የአበባ ጉንጉን ያኖራሉ፤ሩዋንዳውያንም ላጧቸው ወገኖቻቸው ሃዘናቸውንና አክብሮታቸውን ይገልፃሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም