ታዳጊ ሴቶችን ለማብቃትና ደህንነታቸውን ለማስጠበቅ የግልና የጋራ ኃላፊነትን መወጣት እንደሚገባ ተጠቆመ

69

አዳማ መጋቢት 28/2011 ታዳጊ ሴቶችን ለማብቃት፣ደህንነታቸውን ለማስጠብቅና ስብእናቸውን ለመቅረፅ ሁሉም አካል የግልና የጋራ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር አሳሰበ።

" ጀግኒት ጀግኒትን ትቀርፃለች"  በሚል መሪ ሀሳብ የታዳጊ ሴቶች ማነቃቂያ ሃገር አቀፍ መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።

በሚኒስቴሩ የሴቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ስመኝ ውቤ በወቅቱ እንደገለፁት መንግሥት የታዳጊ ሴቶችን የትምህርት ተሳትፎና ስኬታማነታት ለማሳደግ  እየሰራ ነው።

ለታዳጊ ሴቶች የስነ-ተዋልዶ ጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እንዲሁም ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችና ጥቃት የተጠበቁ እንዲሆኑ ለማስቻል የህግና የፖሊሲ ማዕቀፎች ተቀርፀው ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል ።

ይሁን እንጂ ታዳጊ ሴቶችን ከቤተሰብ ጀምሮ እየኮተኮቱ ከማብቃት አኳያ  በርካታ ተግዳሮቶች እንደሚያጋጥሙ ጠቅሰዋል፡፡

ከጠቀሷቸው ተግዳሮቶች መካከል በቤተሰብና ማህበረሰብ ደረጃ ሴት ልጆችን ዝቅ አድርጎ መመልከት፣ ወደ ትምህርት ቤት አለመላክና ተገቢውን ድጋፍ አለማድረግ፣የቤት ውስጥ የስራ ጫና ማብዛት፣ጥቃቶችና ትንኮሳዎች ይገኙበታል።

ችግሮቹን ለመከላከልና ለመቀነስ እንዲሁም ያላቸውን እምቅ ችሎታ እንዲያወጡና አስተዋጽኦቸውን ማበርከት እንዲችሉ ለማብቃት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣የማህበረሰብ አደረጃጀቶችና ቤተሰቦች ለጥረቱ ስኬት የግልና የጋራ ኃፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

በሚኒስቴሩ የሴቶች ንቅናቄና ተሳትፎ ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ታደሰ በበኩላቸው የመድረኩ ዓላማ የሴቶችን ለጥቃት ተጋላጭነት በመቀነስ ስኬታማ እንዲሆኑ የባለድርሻ አካላትን ተነሳሽነት መፍጠር መሆኑን ተናግረዋል።

በዘርፉ የተዛቡ አመለካከቶች እንዲስተካከሉ ምቹ ሁኔታ መፍጠርም ሌላው የመድረኩ ዓላማ እንደሆነ አመልክተዋል።

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ወይዘሮ ፀሐይ መንክር ፣የኢትዮጵያ አየር መንገድ ረዳት አብራሪ ማርታ ነጋሽ እና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሽን ልማት ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሪት ሌሊሴ ነሜ ተሞክሯቸውን በመድረኩ አቅርበዋል።

አቅራቢዎቹ ተሞክሯቸውን መነሻ በማድረግ ታዳጊ ሴቶች ተግዳሮቶችን በመቋቋም ዓላማና ግባቸውን ለማሳካት እንዲተጉ መልዕክታቸውን  አስተላልፈዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም