የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ተመሳሳይ ርዕዮተ ዓለም የሚከተሉ ፓርቲዎች መሰባሰብ አለባቸው

66

አዲስ አበባ መጋቢት 28/2011 የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት የዜጎችን መሰረታዊ ጥያቄዎች ለመመለስ ተመሳሳይ ርዕዮተ ዓለም የሚከተሉ ፓርቲዎች መሰባሰብ እንዳለባቸው ተነገረ።

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሁን በሚመሰረቱበት ዘርን መሰረት ባደረገ የዘውጌ ፖለቲካ የኅብረተሰቡን ጥያቄ መመለስም ሆነ የፖለቲካ ምህዳሩን የማስፋት አቅም እንደማይኖራችውም ተገልጿል።

በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅና አግኝተው የሚንቀሳቀሱ 66 አገር አቀፍና ክልላዊ ፓርቲዎችን ጨምሮ በአገሪቱ 108 ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይገኛሉ።

አብዛኞቹ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመሳሳይ ርዕዮተ ዓለም የሚከተሉና ዘርን መሰረት ባደረገ የፖለቲካ አደረጃጀት መመስረታቸውም ነው የተገለጸው።

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት /መኢአድ/ ከፍተኛ አመራር አባል አቶ አብርሃም ጌጡ ለኢዜአ እንዳሉት ባለፉት ዓመታት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አቅም ፈጥረው በምርጫ እንዳያሸንፉ ትንንሽ ፓርቲዎች እንዲበዙ ሲደረግ ቆይቷል።

ለአገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር መጥበብ ከገዥው ፓርቲ በተጨማሪ ለገንዘብ ሲሉ ብቻ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን የሚመሰርቱ ግለሰቦች ሚናም የጎላ እንደነበር ተናግረዋል።

አሁን ገዥው ፓርቲም ሆነ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይዘውት ከመጡት የተሳሳተ አስተሳሰብ በመውጣት ለህዝቡ የሚመጥን ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲ ምስረታ ላይ ማተኮር እንደሚገባም ነው የገለጹት።

የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት አንድነቷ የተጠበቀ ጠንካራ አገር ለመገንባት የፖለቲካ ፓርቲዎች በዘር ከመደራጀት ይልቅ የህዝቡን ፍላጎት ቢያዳምጡ የተሻለ እንደሚሆንም አክለዋል።

የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኤፍሬም ማዴቦ የዘር ፖለቲካ በመፍረስ ላይ ያለውና ባለፉት 27 ዓመታት ሲቀነቀን የነበረው ከፋፋይ የፖለቲካ ስርዓት ያመጣው ሳንካ ነው ይላሉ።

የመንግስትን መዋቅር ተጠቅሞ ግዙፍ ፓርቲ የሆነውን ኢህአዴግ በምርጫ ለማሸነፍ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ አንድ በመሰባሰብ አቅማቸውን ማጎልበት እንዳለባቸው በመጠቆም።

"በአሜሪካና በጀርመን የሚገኙ ፓርቲዎች አሁን ላሉበት ጥንካሬ የበቁት ከ150 ዓመት በፊት በጀመሩት እርሾ በመሆኑ እኛም ይህንን ታሪክ በሀገራችን መስራት ይጠበቅብናል" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የሰጡትን ማበረታቻ በመጠቀም ከኢህአዴግ የተሻለ አማራጭ ማቅረብና በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች መወዳደር የሚያስችል ጠንካራ አገር አቀፍ ፓርቲ መመስረት እንደሚገባም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ኢዴፓ/ ሊቀ መንበር ዶክተር ጫኔ ከበደ በኢትዮጵያ የሚመሰረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች አጀንዳ የጨቋኝና ተጨቋኝ ትርክት መሆኑን ይገልጻሉ።

"የእኔ ብሄር ተበድሏል፣ በማንነቴ ፍትህ ተጓድሎብኛል፣ እገሌ የሚባለው ብሄር ጨቁኖኛል በሚል የመፈራረጅ ፖለቲካ ዴሞክራሲ ማስፈን ስለማይቻል ከዚህ እኩይ የፖለቲካ አካሄድ መውጣት ይገባል" ነው ያሉት።

ኢዴፓን ጨምሮ ስድስት ፓርቲዎች በአንድነት ለመዋሃድ የሚያደርጉት ጥረት በቀጣይ ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲ መመስረት የሚያስችል ማሳያ መሆኑንም ገልጸዋል።

አገር አቀፍም ሆነ ክልላዊ ፓርቲዎች ልዩነቶቻቸውን በማጥበብ በጋራ መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ በመጣመር፣ በመቀናጀት፣ ወይም በመዋሃድ ብቁና ተወዳዳሪ ሆኖ መቅረብ ያስፈልጋል ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም