ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር የዴሞክራሲ መሰረት እንደሆነ የኢትዮጵያና ኬንያ መሪዎች ገለጹ

96
ናይሮቢሚያዝያ 30/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ለሰላማዊ የስልጣን ሽግግር የአፍሪካ መሪዎች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቀረቡ። ሁለቱ መሪዎች በናይሮቢ ብሔራዊ ቤተ_መንግስት ባደረጉት የሁለትዮሽ ውይይት በአፍሪካ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዲለመድ የበኩላቸውን ሚና እንደሚጫወቱ አስታውቀዋል። መሪዎቹ በአገራቸው ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ባህል እንዲዳብር አበክረው እንደሚሰሩና በአህጉሩ መልካም እሳቤ እንዲጎለብት የጋራ ጥረት እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል። ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ለአፍሪካ አስፈላጊ መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በስልጣን ላይ ያሉ የአፍሪካ መሪዎች በአህጉሪቱ ዘላቂ የሆነና ቀጣይነት ያለው ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዲከናወን የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ጠይቀዋል። "በኢትዮጵያና በኬንያ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ማከናወን አስቸጋሪ አለመሆኑን ለህብረተሰቡ አሳይተናል። ይኸው ተግባር ለመጪው ትውልድ ሊተላለፍ ይገባል። መጪው ትውልድ ይህንኑ ታሪክና ራዕያችንን በመረዳት እንዲሁም የአፍሪካ መስራች የሆኑትን አባቶቻችንን ህልም ተግባራዊ ለማድረግ ጠንክረው በመስራት አፍሪካን ወደ አንድ ከፍታ ማሸጋገር አለባቸው ብለዋል።" ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ቀደም ብለው ለአገራቸው ህዝብ ባደረጓቸው ንግግሮች "የመሪዎችና የከፍተኛ ባለስልጣናት የስልጣን ጉጉት ዴሞክራሲንና ሰላማዊ የስልጣን ሽግግርን የሚያደናቅፍ መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል።" በኢትዮጵያ የአንድ ጠቅላይ ሚኒስትር የስልጣን ዘመን በህግ የተገደበ እንዲሆን እንደሚሰሩ መናገራቸው ይታወሳል። ከዚህ ባለፈ በኢትዮጵያ ስልጣንን የሙጥኝ ብሎ መዝለቅ ማከተሙንም ግልጽ አድርገዋል። ይህንኑ በህግ ማዕቀፍ የጸና ለማድረግ በህገ መንግስቱ እንደሚካተትም ቃል መግባታቸው የቅርብ ጊዜ እውነታ ነው። መሪዎቹ የቀደሙ የአፍሪካ ህብረት መስራች አባቶችን ራዕይ ለአህጉሪቱ ህዝቦች ጥቅም ሲሉ እውን ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰሩም አስታውቀዋል። የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በበኩላቸው የአፍሪካ ህብረት መስራች አባቶችን ራዕይ እውን ለማድረግ የአፍሪካ አገሮች በትኩረት መስራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል። ከአፍሪካ ህብረት መስራች አባቶች መካከል ቀዳማዊ ኃይለስላሴ፣ ጆሞ ኬንያታ፣ ክዋሜ ንክሩማና ጁሊየስ ኔሬሬ የሚጠቀሱ ሲሆን ለዘመኑ ትውልድ የአህጉሪቱን አንድነትና የመጪው ዘመን እድገት መሰረት ማስቀመጣቸው የሚጠቀስ ተግባራቸው ነው። ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ "ህብረት ለአህጉሩ ብልፅግና መሰረት መሆኑን" አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። "የአፍሪካ መፃኢ እድል በእኛ ህብረት ላይ የተመሰረተ ነው ለህዝባችን ቀጣይ ብልጽግና መዋዕለ ንዋያችንን በጋራ ማፍሰስ ይገባናል። የአፍሪካ መስራች አባቶቻችንን ራዕይ እውን ማድረግ እንደምንችል ሙሉ እምነት አለኝ ብለዋል።"
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም