መሪ ማነው!!!

489

በሃብቱ ተሰማ( ኢዜአ)
ለአንድ ሀገር እድገት የሁሉም ተሳትፎ ወሳኝ ነው፡፡ በልማቱም ሆነ በጥፋቱ ተጠያቂው እያንዳንዱ ሰው ቢሆንም ተሳትፎውን በማቀጣጠል የመሪዎች ሚና ጉልህ መሆኑን ምሁራን ያስረዳሉ።
መሪነት በበጎ ተጽእኖ ህብረተሰብን በመቅረጽ በፍቃዳቸው እንዲከተሉ ማድረግ ተቀዳሚ ስራው እንደሆነ በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የሊደርሽፕ መምህር ዶክተር ዋቅጋሪ ነገሪ አብርተዋል። እንደ እሳቸው ሙያዊ ገለጻ የመሪነት ትኩረት ስርአትን በመዘርጋት ሁሉም ህዝብ ለሀገር እድገት የሚተጋበትን አቅም መፍጠር ነው፡፡ ለተግባራዊነቱም የሀገሪቱን ነበራዊ ሁኔታ በመረዳት ሀገር በቀል እውቀትን ከአለም አቀፍ ሁኔታ ጋር አዛምዶ መስራትም አንዱ የመሪ ሚና ነው።

ለሌሎች ሀገሮች የሰራ ቀመር ለኛ ይሰራል ብሎ በቀጥታ መተግበር ከእድገት ይልቅ ውድቀትንም ሊያስከትል ይችላልና።
ከትልቁ ድምጽ ውስጥ ትንንሾችን አድምጦ ወቅታዊ ምላሽ ለመስጠት የመንግስት መዋቅር መጠናከርና ተተኪ መሪዎችን ማፍራት የስኬታማ መሪ ትልቁ መለያ እንደ ሆነ ይናገራሉ ዶክተር ዋቅጋሪ፡፡

መሪዎች በተቀመጡበት ኃላፊነት የሚጠበቅባቸውን ውጤት በማምጣት ለሌሎች ማሳለፍ ሲገባቸው በአንድ ቦታ ለረጅም ግዜ መቀመጥ ስህተትን እንኳ ጥሩ አድርጎ ለማሰብ መንገድ ይከፍታል ይላሉ፡፡ መሪ ካለፈው ግዜ መልካሙን በመውሰድ ደካማውን ማረምና ለቀጣይ ስራ አቅም የሚሆን መሰረት መጣል ተቀዳሚ ስራው እንደሆነም በመግለጽ፡፡
በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የማኔጅመንት መምህር ዶክተር ኃይለ ሚካኤል ሙሌ መሪነት ከሀገር እስከ ቤተሰብ መምራትንያጠቃልላል ይላሉ። ጥሩ መሪ ወቅታዊነት፣ ተገቢነት፣ ተነሳሽነት፣ ቆራጥ ውሳኔ መስጠት መገለጫዎቹ ናቸው፡፡ በተለይም በመሪና ህዝብ መካከል መተማመን መፍጠር የመሪዎች ቀዳሚው ክህሎት እንደሆነም ነው የሚገልጹት።

ሀገር በመገንባት ሂደት የሚከሰቱ መልካምና መጥፎ መንገዶችን ህዝብ በማስተባበር ማረምና ሀገርን ለትውልድ ማሻገርም የመሪ ግዴታ ነው። በታሪክ ቅብብሎሽ የሚከሰቱ ድክመትን ለማረም በተደረገው ጥረት ሀገራችን በርካታ የታሪክ ክዋኔዎችንና የመሪዎች ሚናን አሳልፋለች፡፡
ባለፉት ሶስት አመታት በተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞ ወደ ለውጥ ስለገባው የኢህአዴግ መንግስት የለውጥ አንድምታ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ምሁራን የየራሳቸውን እይታ አላቸው።
“ኢህአዴግ 100% አሸነፍኩ” ባለበት ማግስት ነውጥ መከሰቱና ድርጅቱ ጥልቅ ተሃድሶ ገባሁ ቢልም ችግሩን ለመፍታት ስኬታማ ባለመሆኑ፤ ህዝባዊ ተቃውሞው ቀጥሎ ህዝብ በለውጥ የተቀበላቸውን ዶክተር ዐቢይ አህመድን ወደ ስልጣን እንዲመጣ አድርጓል ያሉት የኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ ንቅናቄ ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት ናቸው።
“በለውጡ እስረኞች ተፈተዋል፤ በሽብርተኝነት ተመዝግበው የነበሩ ሰዎች ወደ ሀገር ገብተዋል፤ መገናኛ ብዙሃን ነጻነት ተሰጥቷቸዋል፤ ይህ ነገር በራሱ የሀገሪቱን ችግር ይፈታል ባይባልም ተስፋ አሳይቷል” ነው ያሉት።
“ከለውጡ በፊት የተለየ ሀሳብ ማንሳት ራስን ለአደጋ ያጋልጥ ነበር፤ አሁን የትኛውም ፖለቲከኛ፣ የሚዲያ ሰው፣ የሲቪክ ማህበር ባስቀመጠው የሀሳብ ልዩነት አይገደልም፤ አይከሰስም፤ አይታሰርም፤ በህገመንግስቱ የተቀመጡት የመናገር፣ የማሰብና የመጻፍ የሀሳብ ነጻነቶች መከበራቸው” ለውጡ ያመጣው መሆኑን ያነሱት ደግሞ የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮ ናቸው።
ኢህአዴግ ከለውጡ በፊት የነበሩበትን በርካታ ችግሮች በጥልቅ ተሃድሶ ግምግሞ ወደ ለውጥ መግባቱን የግንባሩ የህዝብና የውጭ ግንኙነት ዘርፍ ሃላፊ አቶ ሳዳት ነሻ እንዲህ ሲሉ ነው የገለጹት፤ “ይህ ሀገር ዴሞክራሲን ካላረጋገጥን ሀገር ሆኖ መቀጠል የማይችልበት ደረጃ እየደረሰ ስለሆነ፤ በተጨባጭም ስላየነው ከለውጡ በፊት ባለፉት 3 እና 4 ዓመታት ህብረተሰቡ በሚገባ የሚደግፈውንና የሚነቅፈውን በግልፅ የሚያቀርብበት ሁኔታ ባለመመቻቸቱ እንደ ድርጅትም እንደ ሀገርም ዋጋ ከፍለናል”።
የለውጥ ገጽታዎች
ለውጥ በታቀደና በድንገት ይከሰታል፡፡ ለውጡ መሰረት እስኪይዝም ያለመረጋጋት መከሰቱ ተፈጥሮአዊ እንደሆነም የሚነግሩን ዶክተር ሀይለሚካኤል በኛ ሀገር የለውጥ ሂደትም የፍትህና የስራ አጥነት ጥያቄዎች ጎልተው በመውጣት በአጭር ግዜ ለውጥ መምጣቱ ይህን መሰል አለመረጋጋት መከሰቱ ተፈጥሮአዊ ነው ይላሉ፡፡

የለውጡን አቅጣጫ ለማስቀመጥ፤ መንግስት የኢኮኖሚ፣ የስራ አጥነትና የመዋቅር የፍትህ ጥያቄዎችን ከመመለሱ በፊት መጀመሪያ የሀገርን ሰላም ማስፈን መቅደም እንዳለበትም ዶክተር ሀይለሚካኤል ምክረሃሳብ ይሰጣሉ ፡፡
የለውጡ ፈተናዎችና የተቋማት ግንባታ
ተቋማት የሚገነቡት ወይም የሚታጠፉት በጥናት መሆን አለበት የሚሉት ዶክተር ዋቅጋሪ ይህን የሚቃረን አሰራር፤ ስርአትን በመገንባት የአንድ ሀገር እድገት ቀጣይነት ያለው እቅድና ፖሊሲ ቀርጾ ህዝብ የሚሳተፍበትን አቅም መፍጠር አያስችልም ነው ያሉት። በሀገራችንም ለውጡን ተከትሎ መንግስት የጀመራቸው የተቋማት የለውጥ ስራዎች የተሻለ መንገድ እንደሚፈጥሩ እምነታቸውን በመግለጽ፡፡
ዶክተር ሃይለሚካኤል እንደሚሉት ከለውጡ በፊት ህብረተሰቡ የሚመለከታቸውን አመራሮች አሁንም በቅርበት ማየቱ ለውጡ ታች አልደረሰም ብሎ አስረጅ አድርጎ ማሰቡ ሁለት መልክ አለው፡፡
ከለውጡ በፊት ለሀገር የሚጥሩ አካላት የመኖራቸውን ያህል አጥፊዎችም አሉ፡፡ ይህን ባለመረዳት ሁሉን ነገር ስር ነቀል ማድረግ ያለውን መልካም እርሾ ጭምር ስለሚያጠፋ መንግስት ችግሩን በሚዛኑ በማየት የሙስናና መልካም አስተዳደር ችግር የፈጠሩ አካላት ላይ የወሰደው እርምጃ መልካም ጅምር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የለውጡን ሂደት ዳር ለማድረስ ህዝብ የመንግስትን እርምጃ በትዕግስት የመጠበቅ ግዴታ እንዳለበትም በማስረዳት፡፡
ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት “ኢህአዴግ የኢትዮጵያን ለውጥ መሸከም የሚችልበት አቅም ላይ አይደለም፤ የግንባሩ እህት ፓርቲዎች የኔነው በሚሉት ጉዳይ ላይ ብቻ አተኩረዋል፤ ሁሉም በመጠራጠር ላይ ናቸው አደገኛ ሁኔታ ላይ ነን፤ ኢትዮጵያን የሽሚያ ሀገር አድርገውታል” በማለት ትዝብታቸውን ገልጸው፤ ይሄም የለውጡን ቅቡልነት አደጋ ላይ ጥሎታል ብለዋል።
አቶ ተሻለ ሰብሮ “አንዳንዶቹ አክቲቪስት ወይስ ፖለቲከኛ መሆናቸውን አናውቅም፤ ህዝብን እየከፋፈሉ ነው፤ በሰላማዊ መድረክ በመነጋገር ልዩነቶችን ማጥበብ እንጂ ኢትዮጵያን ስጋት ላይ የሚጥል መጥፎ ድርጊት መስራት አይገባም” ይላሉ።
“ፓርቲዎች በየቦታው እንደ አሸን እየፈላን ህዝቡን ልንከፋፍል አይገባም፤ ህዝቡም ተባብሮ ጥራት ያለው ሃሳብ የያዙ ፓርቲዎች እንዲመሰረቱ፣ ወደ መሰባሰብ እንዲመጡ መስራት ይገባል። አንዳንዶች ለዝና፣ ለመዝናናት፣ ለመተዳደሪያነት፣ አንዳንዶች በትክክል ህዝብን ለማገልገል ነው ፓርቲ የመሰረቱት” በማለትም አስተያየታቸውን ያካፈሉን።
ተቀራራቢ ሀሳብ ያላቸው ፓርቲዎች ተዋህደው ግንባር በመፍጠር ርዕዮተ ዓለምና እቅዶችን አቻችለው መስራት አለመቻላቸውና መንግሥትም ጸጥታንና ህግን የማስከበር ሃላፊነቱን በሚገባ መወጣት አለመቻሉ ለውጡን ስጋት ላይ ጥሎታል በማለት ነው ያስረዱት፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ የህዝቡ እርካታ ከነበርንበት ሁኔታ አንጻር ሁሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲያነጋግራቸው፤ መልስ እንዲሰጣቸው የሚያነሱትን ጥያቄዎች በተቻለ መጠን ምላሽ ለመስጠት ተሞክሯል የሚል ሀሳብ አለኝ የሚሉት ደግሞ አቶ ሳዳት ናቸው።
“ይህ እንዳለ ሆኖ በየደረጃው ያለ አመራር የሚሰጠውን መልስ ህዝብ አመኔታ የማጣት ችግሮች፣ በተሃድሶ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ አዲስ ፊት መፈለግ ና ነባሮችን ሁሉ በጥርጣሬ ለማየት ና አለማድመጥ በመታየቱ ይህን በውይይት እየፈታን ነው” በማለትም አሁን እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችን ያብራራሉ።
በአመራር ደረጃም በራስ በመተማመን መልስ የመስጠት ክፍተት መኖሩ፤ይሄም ህብተረሰቡ በተወሰነ አመራር ላይ እምነት ሲያሳድር በሌሎች ላይ ጥርጣሬ መፈጠሩን አቶ ሳዳት አልሸሸጉም፤ በሂደትም ችግሩን ለመፍታት መሰራቱን በማስረገጥ ፡፡
በእስካሁኑ ሂደቶች መሪዎች ህብረተሰቡን መቅረጽ ባለመቻላቸው በየግዜው ለሚከሰቱ ችግሮች ሁሉም ወደ ራሱ አቅጣጫ ህዝቡን በመጎተቱ ችግሩ ቀጥሏል ያሉን ዶክተር ሀይለ ሚካኤልናቸው። ይህ ድርጊት ህዝብን ለመጥቀም ሳይሆን ዝም ለማሰኘት በየፊናቸው አላስፈላጊ ቃላትና መግለጫ በማውጣት ህዝብን በማደናገር ለውጡን ጥርጣሬ ውስጥ በመክተት ሀገሪቷ ወደኃላ እንዳትመለስ ቆም ብሎ ማሰብ እንደሚገባም መክረዋል ፡፡
በአሁኑ ሰአት በየቦታው የሚታዩ አለመግባባቶች የራሳቸው ጉዳት ቢኖራቸውም ችግሩን በተገቢው አጥንቶ ዘለቄታዊ መፍትሄ ለማስቀመጥ መነሻ ሊሆኑ እንደሚችሉ ሀሳብ ያካፈሉን ዶክተር ሀይለሚካኤል፤ ችግሩ ከቁጥጥር ሳያልፍ ወቅታዊ ምላሽ መስጠትም ከመቼውም ግዜ በላይ ትኩረት ያስፈልገዋል፡፡
ሀገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል
አሁን በኢትዮጵያ የመጣው ለውጥ እንዲሳካ ወጣቱ በስራ ፈጠራ የሚሳተፍበትና ጥያቄዎቹን በምክንያትና በተጠና መንገድ እንዲጠይቅ ማገዝ፣ የማህበረሰብ መሪዎችን፣ ምሁራንና ፓርቲዎች በየሙያቸው የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ በሰፊው ማሳተፍ የቀጣይ ተግባራት መሆን እንዳለባቸው ዶክተር ሀይለሚካኤል መክረዋል፡፡ መንግስትም የግጭት ምንጭን ቀድሞ በማጥናት ህዝብን በማጋጨት የርካሽ ተወዳጅነት አጀንዳ የሚፈጥሩ አካላትን ማሳጣት የሚያስችል መዋቅር ማጠናከር አስገዳጅ መሆኑን በመጠቆም፡፡
“እነዚህንም መንግስት መፍትሄ የሚሰጥበትን ግልጽ አቅጣጫ በማስቀመጥ ህዝብ የሚሳተፍበትንና በትግስት የሚጠብቅበትን እድል ለመፍጠር መወያየት ያስፈልጋል፤ ይህም ነው መንግስት የሚሰራቸውን ተግባራት ህዝብ ያለመረዳት ውስጥ የከተተው” ብለዋል፡፡
ችግሩንም ለመቅረፍ መንግስት በየደረጃው ባለው መዋቅር በአጭርና በረጅም ግዜ የሚፈቱበትን መርሀ ግብር በማሳወቅ፤ ግልጽነት በመፍጠር ህዝቡ እርስ በርስ በመወያየት ለመፍትሄው በጋራ የሚሰራበትን እድል መፍጠር እንደሚያስፈልግም አብራርተዋል።
ኢንጂነር ይልቃል ባነሱት ሃሳብ አመራሮች ችግሩን የሚመጥን መፍትሄ መውሰድ አለመቻላቸው፤ ግለሰቦች ለለውጡ ቢሰሩም መዋቅራዊ አለመሆኑ፣ በየደረጃው ያሉ አመራሮች የአቅምም ሆነ የተነሻሽነት ውስን መሆኑ ለውጡ ህዝቡ ተስፋ ባደረገበት መንገድ ስኬታማ እንዳይሆን አድርጎታል፡፡
“ይህን አውቀንበት የሀገር ውስጥ መፈናቀልን፣ ኢኮኖሚያዊ ችግርን፣ የፖለቲካውንም ችግር ፈትተን መልክ ያለው ነገር እንፈጥራለን፤ በአጫጭር ጊዜ ፍላጎቶች ተሸፍነው ትላልቅ ችግሮች ገዝፈው እንዳያጠፉን በጋራ መስራት አለብን” በማለት ነው ኢንጂነሩ ለለውጡ ዝግጁ መሆናቸውን የተናገሩት።
ኢህአዴግ ችግር ከመፈጠሩም በፊት ሆነ ሲፈጠር ችግር ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት ህብረተሰቡና መንግስት ተቀናጅተው ለመፍትሄ የሚሰሩበት አሰራር መዘርጋቱን ያነሱት አቶ ሳዳት፤ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ውይይት መጀመሩና ቃል ኪዳን ሰነድ መፈራረማቸው አንድ እርምጃ መሆኑን ይገልጻሉ።
የሆነው ሆኖ ለአንድ ሀገር እድገትም ሆነ ውድቀት ትልቅ ሚና ያላቸው መሪዎችና ህዝብ በመሆናቸው አንዱ ከአንዱ ተነጥሎ ለውጥን ብቻ መፈለግ አይታሰብም። በሀገራችን የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠልና የታለመለትን ግብ ለማሳካትም ሀገሪቱን የሚመራው መንግስት፣ በየደረጃው ያለው አመራርና የህብረተሰብ ክፍል ተቀራርቦና ተባብሮ መሥራት ለነገ የሚባል ባለመሆኑ ለለውጡ መሳካት “የእኔም ጥረት” ወሳኝ ነው በሚል መንፈስ ልንሰራ ይገባል። ቸር እንሰንብት!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም