የሀሸንጌ ሃይቅን ከጥፋት ለመታደግ የሚያገዝ የልማት ፕሮጀክት ተጀመረ

101

ማይጨው መጋቢት 28/2011 በትግራይ ደቡባዊ ዞን የሚገኘው የሀሸንጌ ሃይቅን ከጥፋት ለመታደግ ተፋሰስን መሰረት ያደረገ የልማት ፕሮጀክት መጀመሩን የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡

ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ የክልሉ መንግስት ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት  መድቧል፡፡

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ክፍሎም አባዲ  እንዳሉት፣በሃይቅ ዙሪያ ካሉት ተፋሰሶች በየዓመቱ ከአራት ሺህ ቶን በላይ አፈር በጎርፍ ታጥቦ ወደ ሀይቁ  በመግባት በደለል እንዲሞላ ምክንያት ሆኖ ቆይቷል፡፡

የክልሉ መንግስት ሃይቁን ን ከጥፋት ለማዳን ለመጪዎቹ ሶስት ዓመታት የሚቆይ ተፋሰስን መሰረት ያደረገ የልማት ፕሮጀክት በስምንት ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ለማካሄድ እንቅስቃሴ ጀምሯል።

በሀሸንጌ ሀይቅ ከሚካሄደው የልማት ፕሮጀክት መካከል የአፈር መሸርሸርን የሚከላከሉ የክትር፣ የጠረጰዛ ፡ የአፈርና የድንጋይ እርከን ግንባታዎች ይገኙበታል፡፡

እንደ አቶ ክፍሎም ገለጻ ፣ቢሮው ፕሮጀክቱ ግንባታ ማስፈፀሚያ 6 ሚሊዮን ብር በጀት መድቧል።

በተለይ በፕሮጀክቱ ለሚከናወነው የድንጋይ እርከን ግንባታ የሚውል ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ጋቢዮን የተባለ የብረት ሽቦ  ተዘጋጅቷል፡፡

የልማት ፕሮጀክቱን ለማከናወን የሚረዳ ድንጋይ   በአካባቢው ወጣቶች እየቀረበ  መሆኑን የገለጹት ደግሞ በደቡባ ዞን የኦፍላ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ረዳኢ ዝበሎ ናቸው።

በአካባቢው የሚኖሩ 300 ወጣቶች በ11 ማህበራት ተደራጅተው በስራው በመሳተፍ የስራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተመቻችተዋል፡፡

የዞኑ  አስተዳዳሪ አቶ ረዳኢ ሓለፎም በበኩላቸው ሀይቁን ከጥፋት ለመታደግ የሚካሄደው ልማት ዘለቂነትን ለማረጋገጥ ለአካባቢው ስነ-ምህዳር ተስማሚ የሆኑ የእፅዋት ዝርያዎችን የማልማቱ ስራ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አመልክተዋል።

በተለይ የአፈር መከላትን በመከላከል ተጨማሪ የምጣኔ ሀብት  ጥቅም የሚያስገኝ የቀርቀሃ እፅዋት በሀይቁ የተፋሰስ ልማት በስፋት እንዲከናወን መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ሀይቁ በደለል እየተሞላ በመምጣቱ  በእንስሳት እርባታው ላይ የሚያስከትለውን ችግር ለመከላከል በአፈርና ውሃ ጥበቃው ስራ እየተሳተፉ መሆናቸውን የገለጹት በኦፍላ ወረዳ የመንከረ ቀበሌ አርሶ አደር ሃፍቱ ግደይ ናቸው፡፡

በዚሁ ቀበሌ ወጣት አርሶ አደር ግርማይ ነጋሽ  በበኩሉ  ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር በማህበር ተደራጅቶ በሃይቁ የልማት ፕሮጀክት እየተሳተፈ ሀብቱን ከጥፋት ለመጠበቅ  የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ተናግሯል፡፡

በልማቱ የስራ እድል ተጠቃሚ እንደሆነም ጠቁሟል።

ከዚህ ቀደምብሎ  በሃይቅ ዙሪያ በአካባቢው ህዝብ የጉልበት ተሳትፎ ለ20 ቀናት ሲካሄድ የቆየው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ  የተጠናቀቀ ሲሆን በዚህም የላቀ አስተዋፅኦ ለበረከቱ ሞደል አርሶአደሮች  የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም