የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤውን ከነገ ጀምሮ ያካሂዳል

70

ሰመራ መጋቢት 28/2011 የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት 5ኛ ዙር 4ኛ የሥራ ዘመን 8ኛ መደበኛ ጉባኤውን ነገ በሰመራ ከተማ ማካሄድ እንደሚጀምር የክልሉ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

ጉባኤው ለሦስት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን የአስፈጻሚ አካላትን የ6 ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት አድምጦ እንደሚወያይና የተለያዩ አዋጆችን መርምሮ እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል።

የአፋር ክልል ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አሊሚራህ ሙሳ እንደተናገሩት ምክር ቤቱ ጉባኤን የሚያካሂደው ከነገ ጀምሮ ለተከታታይ 3 ቀናት ነው።

"በጉባኤውም የአስፈጻሚ አካለትን የ6 ወራት ሪፖርቶችና የተለያዩ አዋጆች ላይ ተወያይቶ እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል" ብለዋል።

በተለይ የክልሉ ምክር ቤት ሕብረተሰቡ በየደረጃው የሚያነሳቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት በአስፈጻሚ አካላት ባለፉት 6 ወራት የተከናወኑ ተግባራት ላይ ይበልጥ ትኩረት ሰጥቶ ሰፊ ውይይት እንደሚያደርግ አመልክተዋል።

በተጨማሪም በሀገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ በክልሉ ተቋማዊ አደረጃጀት ኑሮት ወደታች ለማውረድ የሚያግዙ የተለያዩ ማሻሻያ አዋጆች በምክር ቤቱ  እንደሚጸድቁ አቶ አሊሚራህ ተናግረዋል።

በምክር ቤቱ ይጸድቃሉ ተብሎ ከሚጠበቁ አዋጆች መካከል የክልሉ የብዙሃን መገናኛ ለማቋቋም የሚያስችል ረቂቅ አዋጅና የክልሉን ስራ አመራር ኢንስቲትዩት ወደአካዳሚ ደረጃ ለማሳደግ የሚያስችል ማሻሻያ አዋጆች ይገኙበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም