ግጭትና ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ቀንሷል - የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት

83

አዲስ አበባ መጋቢት 27/2011 በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ይከሰቱ የነበሩ ግጭቶችና ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ባለፉት ስድስት ወራት መቀነሱን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ገለጸ።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህና በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ዛሬ ለአገር ውስጥና ለውጭ አገር ጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።

አማካሪ ሚኒስትሩ በተለያዩ አካባቢዎች ላይ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን በሚል ካለፉት ስድስት ወራት ወዲህ ነገሮችን በጥንቃቄ በመከታተል ግጭት መቀነስ ተችሏል ነው ያሉት።

በየአካባቢው ችግር ከመፈጠሩ በፊት የአካባቢ አመራሮች ህዝቡን እንዲያወያዩ ሲደረግ እንደነበርም አውስተዋል።

የተለያየ አመለካከት ባላቸው የፖለቲካ ኃይሎች በትጥቅ ትግል ጭምር ስልጣን የመያዝ ፍላጎትና ህዝብ ከህዝብ በማጋጨት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚሰሩ አሉ ብለዋል።

ህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርም ባለፉት ስድስት ወራት መቀነሱን ያነሱት አማካሪ ሚኒስትሩ የመረጃ አካላት ትስስርና በጋራ የመስራት ልምድ ይበልጥ እየዳበረ ሲመጣ የበለጠ ይቀንሳል ብለዋል።

ቀደም ሲል ህገ-ወጥ መሳሪያ በተሽከርካሪ ቦቴዎች ጭምር ከቦታ ቦታ ሲዘዋወር እንደነበር አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም