በክልሉ ህዝባዊነትን የተላበሰ የፖሊስ ኃይል የመገንባት ተግባር ቅድሚያ ተሰጥቶት ይሰራል---ኮሚሽነር አበረ አዳሙ

58

ባህርዳር መጋቢት 27/2011 በክልሉ ወንጀልን ለመከላከል ህዝባዊነትን የተላበሰ የፖሊስ ኃይል የመገንባት ተግባር ቅድሚያ  ተሰጥቶት የሚሰራ መሆኑን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር አበረ አዳሙ ተናገሩ።    

ኮሚሽኑ ከሁሉም የክልሉ ዞኖችና ሶስት የከተማ አስተዳደሮች  ከተውጣጡ የፖሊስ መምሪያ ኃላፊዎች ጋር በወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ ዙሪያ ዛሬ በባህርዳር ከተማ ተወያይቷል።

ኮሚሽነሩ በውይይቱ ወቅት እንደተናገሩት የክልሉን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ የህዝብን አደራ ተሸክሞ በቁርጠኝነት ተግቶ የሚሰራ የፖሊስ አባል ያስፈልጋል፡፡

ለዚህም የፖሊስ ኃይሉን አቅም በመገንባት በራሱ የሚተማመን፣ ህዝባዊነትን የተላበሰና ሳይንሱን ቀድሞ የተረዳ የፖሊስ ኃይል ለመገንባት በቀጣይ እንደሚሰራም ገልጸዋል።

ይህም በየአካባቢው የሰው ህይወት እንዳይጠፋ፣ ንብረት እንዳይወድም የፖሊስ ኃይሉ ወጥ የሆነ የወንጀል መከላለልና ህግ የማስከበር ስራውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ያስችለዋል።

በየደረጃው የሚገኙ የፀጥታ ተቋማት  ቅንጅታዊ አሰራር ፈጥረው በመንቀሳቀስ የክልሉን ህዝብ ሰላምና ደህንነት በዘላቂነት እንዲጠብቁ ያግዛል።

" የወንጀል መንስኤዎችን ቀድሞ በመለየትና በማክሸፍ ህዝቡን ከፖሊስ ጎን በማሰለፍ ሰላምና ደህንነቱን ማስጠበቅ ይጠበቅብናል " ብለዋል።

በክልሉ እየተስተዋለ ያለውን አንፃራዊ ሰላም ዘላቂነት እንዲኖረው ቀን ከሌት በጋራ መስራት እንደሚገባም  ኮሚሽነሩ አሳስበዋል፡፡

የሰሜን ሸዋ ዞን ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ፍቅሩ ሳህሌ በበኩላቸው የዞኑ የፀጥታ ኃይል መደበኛ የህግ ማስከበር ስራውን ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ሀገሪቱ ለውጥ ላይ ያለች ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የዞኑ ህዝብ ይህንን እየደገፈና እያበረታታ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራና ኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ በሆነው ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አራት ቀበሌዎች በቡድንና በትጥቅ የተደገፈ ግጭት ተከስቶ እንደነበርም አስረድተዋል።

ችግሩን ለመፍታትና የአካባቢው ሰላም ወደነበረበት ለመመለስ  የሁለቱ ክልል መንግስታት የፀጥታ ተቋማት በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

መደበኛ ፖሊስ፣ የአድማ ብተና፣ ልዩ ኃይልና ሌሎችም የፀጥታ ኃይሎች ሰላምን ለማስከበር ኮሚሽኑ በአግብቡ ተመልክቶ የማቀናጀት ስራ ማከናወን እንዳለበትም ጠቁመዋል።

በዞኑ ከጥቅምት 24/2011 ዓ.ም. ጀምሮ በአማራና በቅማንት ብሄረሰቦች መካከል ተፈጥሮ በነበረው ግጭት በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን የገለጹት ደግሞ የምዕራብ ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያ ተወካይ ዋና ኢንስፔክተር አባይ አሻግሬ ናቸው፡፡

የመከላከያ ሰራዊት፣ ፌዴራል ፖሊስ፣ የክልሉ አድማ ብተናና ሌላውም የጸጥታ ኃይል ተቀናጅተው እየሰሩ በአሁኑ ወቅት የዞኑ ሰላም ወደነበረበት መመለሱን አስታውቀዋል።

በተለይ ከሁለቱ ወገኖች የተወጣጡ የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ዕርቅ እንዲያወርዱ ማድረጋቸውን አመልክተው " እርቁን ወደህዝቡ ለማውረድም እየተሰራ ይገኛል "ብለዋል።

ለግጭቱ መቀስቀስ ምክንያት ናቸው ተብለው በመጠርጠር ሲፈለጉ ከነበሩ ሰዎች መካከል 110 ተይዘው ጉዳያቸው በፍርድ ሂደትና በምርመራ ላይ መሆኑንም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም