ኢንዱስትሪዎች የመጪውን ትውልድ ዕድልና የአገሪቱን ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚ የሚያረጋግጡ መሆን አለባቸው

56

አዲስ አበባ  መጋቢት 27/2011በግንባታ ላይ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች የመጪውን ትውልድ ዕድልና የአገሪቱን ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚ የሚያረጋግጡ መሆን እንዳለባቸው የደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን አስታወቀ።

የኦሮሚያ ክልል የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ በለስልጣን ከፌዴራል የደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ጋር በመሆን የአየር ብክለትን በመቀነስ ለውጥ እያመጡ ላሉ ኢንዱስትሪዎችን እውቅና ሰጥተዋል።

ከክልሉና ከፌዴራል የደንና አየር ንብረት ኮሚሽን የተውጣጡ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በአዲስ አበባ ዙሪያና በቢሾፍቱ የሚገኙ የተመረጡ ኢንዱስሪዎችን ትናንት የጎበኙ ሲሆን ለ18 ኢንዱስትሪዎች የእውቅና ምስክር ወረቀትና ዋንጫ ተበርክቷል።

የደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ እስካሁን በአገሪቱ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች የመጪውን ትውልድ የመልማትና የመኖር ህልውና የሚጎዱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ይህን ተከትሎ መንግስት ተበታትነው የሚገኙትን በኢንዱስትሪ ዞን በማሰባሰብ የተረፈ ምርት ማጣሪያ በጋራ እንዲጠቀሙ የማስተሳሰር ፕሮጀክት መጀመሩንም ገልፀዋል።

አሁን ያሉትም ይሁኑ ከዚህ በኋላ የሚገነቡት ኢንዱስትሪዎች ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጥበቃ መስፈርትን ያሟሉ እንዲሆኑና በተፈጥሮ ሃብት ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ጥብቅ ክትትል እንደሚደረግም አስታውቀዋል።

ቀደም ሲል የነበረው ቸልተኝነት እንደማይቀጥልና ችግር ባለባቸው ኢንዱስትሪዎች ላይ እርምጃ የመውሰድ ጥሩ ውጤት የሚያስመዘግቡትን ደግሞ የማበረታታት ስራው ይቀጥላል ብለዋል።

በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል የገጠር ልማትና ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ በበኩላቸው ኢንቨስትመንቱን ከአየር ንብረት ጋር በማጣጣም ዘላቂ ልማት እንዲኖር በመንግስት ሊደረግ የሚገባው ክትትልና ድጋፍ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

በዚህ ረገድ ኢንዱስትሪዎች የአየር ንብረት ያለመበከል ብቻም ሳይሆን ለአካባቢው ማህበረሰብ የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶችን የመስጠት፣ ለሰራተኞች የደህንነት መጠበቂያና የድንገተኛ አደጋ መከላከል መስፈርቶችን ጭምር የማሟላት ግዴታ አለባቸው ብለዋል።

የአየር ንብረት የሁሉም ማህበረሰብ ጉዳይ ስለሆነ በመንግስት በኩል ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የኢንዱስትሪዎቹ ተወካዮች በበኩላቸው የተበረከተላቸው ሽልማትና የተሰጣቸው እውቅና በቀጣይ ትኩረት ሰጥተውን እንዲሰሩ እንደሚያበረታታቸው ተናግረዋል።

መንግስት ሁሉንም ኢንዱስትሪዎች በእኩል የማየት፣ የመከታተል፣ የመቆጣጠር፣ የማበረታታትና ሲያጠፉም እርምጃ የመውሰድ ተግባሩ መጠናከሩ ለማህበረሰቡ ደህንነት ብቻም ሳይሆን ለፍትሃዊ የገበያ ውድድርም ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

ዛሬ እውቅና ከተሰጣቸው ኢንዱስትሪዎች መካከል የአየር ንብረት ብክለትን ከመቀነስ አኳያ የፍሳሽ ማጣሪያ ፕሮጀክት የገነቡና በመገንባት  ላይ ያሉ፣ ለህብረተሰቡ የማህበራዊ አገልግሎት ግዴታቸውን እየተወጡ ያሉና እንዲያስተካክሉ የተነገራቸውን ያስተካከሉ ይገኙበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም