በአሌልቱ ማሰልጠኛ ማዕከል የተከሰተው የጉድፍ በሽታ ወረርሽኝ በቁጥጥር ሥር መዋሉ ተገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
በአሌልቱ ማሰልጠኛ ማዕከል የተከሰተው የጉድፍ በሽታ ወረርሽኝ በቁጥጥር ሥር መዋሉ ተገለፀ
አዲስ አበባ መጋቢት 27/2011 በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በፌደራል ማረሚያ ቤት አሌልቱ ማሰልጠኛ ማዕከል የተከሰተውን የጉድፍ በሽታ ወረርሽኝ መቆጣጠር መቻሉ ተጠቆመ።
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ በ33 ሰልጣኞች ላይ የተከሰተውን የጉድፍ በሽታ በተደረገው ርብርብ ከባድ ጉዳት ሳያደርስ መቆጣጠር ተችሏል።
ከታማሚዎቹ 31 የሚሆኑት ሙሉ በሙሉ ከበሽታው የዳኑ ሲሆን ቀሪዎቹ የባለሙያ ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑም ተመልክቷል።
በቅርብ ቀን ወደ ቀድሞ ጤንነታቸው ይመለሳሉ ሲልም ገልጿል።
ኢንስቲትዩት የጉድፍ በሽታ ወረርሽኝ መከሰቱ ሪፖርት ከተደረገለት በኋላ የበሽታዎች ቅኝት፣ ላብራቶሪ፣ የድንገተኛ ጤና ትምህርት ባለሙያዎችና የቆዳ እስፔሻሊስት ያሉበት የፈጣን ምላሽ ሰጪ ቡድን ወደስፍራው በመላክ ስለበሽታው ምክርና የጤና ትምህርት ተሰጥቷል።
ለበሽታው ተገቢው የባለሙያ ድጋፍ በወቅቱ በመደረጉ የሞት አደጋ አለመከሰቱና ላለፉት አምስት ቀናትም አዲስ ታማሚ ሰልጣኝ አለመኖሩን መግለጫው አመልክቷል።
በሽታው በማሳል፣ በንግግርና በማስነጠስ ጊዜ ከአፍ በሚወጣ እርጥበት ወይም ምራቅ፣ የቆዳ ሽፍዎች ሲቆስሉ ከሚፈጠረው የቁስል ፈሳሽ ጋር በሚኖር ንክኪ ይተላለፋል።
ስለዚህ የማዕከሉ ሰራተኞችና ስልጣኞች በባለሙያ እየተሰጠ ያለውን የጤና፣ ትምህርትና ምክር ሃሳብ ተግባራዊ በማድረግ እራሳቸውን ከበሽታው እንዲከላከሉ ኢንስቲትዩት አሳስቧል።