የደስታ መሰል በሽታን ለመቆጣጠር የዘመቻ ስራ መጀመሩን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ

74

አዳማ መጋቢት 27/2011 የቤት እንስሳትን የሚያጠቃው የደስታ መሰል በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል ዘመቻ መጀመሩን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ለዘመቻው ማስፈጸሚያ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቧል።

በሚኒስቴሩ የእንስሳት  በሽታ መከላከል ዳይሬክተር ዶክተር አለማየሁ መኮንን እንደገለጹት የበሽታው ምልክት በደቡብ ዳሰናችና ያንጋቶም ፣ በአሮሚያ ጉጂና ቦረና እንዲሁም በሶማሌና አፋር አንዳንድ አካባቢዎች ታይቷል፡፡

በሀገሪቱ የቤት እንስሳት ሀብት በስፋት በሚገኝባቸው በእዚህ ክልሎች ይህንን ደስታ መሰል በሽታ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ባለፉት ሶስት ዓመታት  በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ ሲደረግ የቆየው ፕሮጀክት ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል።

የተጀመረው የደስታ መሰል እና ተዛማጅ ድንበር ዘለል የእንስሳት በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ዘንድሮን ጨምሮ እስከ ቀጣዮቹ  አምስት ዓመታት ይቆያል፡፡

ለዚህም ስትራቴጂክ እቅድ ተዘጋጅቷል።

በዚህም ኦሮሚያ፣አማራ፣ትግራይ፣ደቡብ ፣ጋምቤላ፣ቤንሻንጉል ፣ሐረሪ ክልሎችና እና  ድሬደዋ አሰተዳደር በዘመቻው የሚሸፈኑ መሆኑን ዶክተር አለማየሁ አስታውቀዋል።

በተጨማሪም አጎራባች ከሆኑት  ኬኒያ፣ጅቡቲ፣ሶማሊያ ፣ደቡብ ሱዳንና  ሱዳን ጋር በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር   በትብብር እየተሠራ መሆኑን አመልክተዋል።

እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2027 ደግሞ  በሽታውን ሙሉ ለሙሉ ከሀገሪቱ ለማጥፋት ግብ መቀመጡን ጠቅሰው አሁን የተጀመረው ዘመቻ የዚህ አንዱ አካል መሆኑን አስረድተዋል።

ለበሽታ ዳሰሳ ጥናት የሚያግዙ ዘመናዊ የምርመራ ቴክኖሎጂ ማስገባታቸውን ያመለከቱት ዳይሬክተሩ ምርመራው እንስሳቱ ባሉበት የአርብቶ አደሩና አርሶ አደሩ ቄዬ የሚከናወን መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህ  የሚሆኑ በተለይም የኬሚካልና የቤተ ሙከራ  ግብአት መሟላቱን ገልጸው የመቀሌ፣የኮምቦልቻ፣የሂርናና የሰበታ የእንስሳት የጤና ጥበቃ ቤተሙከራዎች ለዘመቻው ሙሉ ድጋፍ ይሰጣሉ ተብሏል።

በዘመቻው ከ60 ሚሊዮን በላይ በጎች ፣ፍየሎችና ዶሮዎች እንዲሁም የዳልጋ ከብት ክትባት እንደሚሰጥ ተመልክቷል።

የዘመቻ ስራውን ማጠናከር በሚቻልበት ዙሪያ ለሁለት ቀናት የተዘጋጀ የውይይት መድረክ በአዳማ ከተማ የተጀመረ ሲሆን ከሁሉም ክልሎች የተወጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎችና አስተባባሪዎች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም