የተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋዎች የማንበብ ክህሎት ዝቅተኛ ነው - ትምህርት ሚኒስቴር

123

አዲስ አበባ መጋቢት 27/2011 የሁለተኛና ሶስተኛ ክፍል ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋዎች የማንበብ ክህሎት ዝቅተኛ መሆኑን በተከታታይ በተካሄዱ ምዘናዎች ማረጋገጡን የትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ በአገር አቀፍ ደረጃ የ2ኛና 3ኛ ክፍል ተማሪዎች የማንበብ ክህሎት ምዘናና የ10ኛ እና የ12 ክፍል ተማሪዎች የትምህርት ቅበላ ጥናት ተካሂዷል።

በአራት ሺህ የ1ኛ ደረጃ 12 ትምህርት ቤቶች በሚገኙ የ3ኛ ክፍል ተማሪዎች የሂሳብ፣ የእንግሊዝኛና የአፍ መፍቻ ቋንቋ ሶስት ጊዜ  የተማሪዎች ብቃት መመዘኛ ተካሂዷል።

85 በመቶ በሚሆኑ የአገሪቱ ተማሪዎች በሚማሩባቸው ቋንቋዎች ላይ በተካሄደ ጥናትም የማንበብ ክህሎታቸው ዝቅተኛ እንደሆነ ተመልክቷል።

እንደ ዶክተር ጥላዬ ገለጻ ከ170 ሺህ በላይ መምህራን በሰባቱ የአፍ መፍቻ ቋንቋዎች የማስተማሪያ ዘዴዎች ላይ ከ10 ሚሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ እንዲሰለጥኑ ቢደረግም በሚጠበቀው መልኩ የተማሪዎች የንባብ ክሀሎት አልዳበረም።

ምዘናው ተማሪዎቹ ዝቅተኛውን ተፈላጊ ችሎታ ማሟላታቸውን፣ በየትኞቹ የትምህርት አይነቶች የተሻለ ውጤት አለ በሚሉት ላይ ያተኮረ እንደነበር ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

በሁሉም የትምህርት አይነት የተያዙ ግቦች አለመሳካታቸውን፣ በተለይም በእንግሊዝኛ ትምህርት የሰፋ ችግር መኖሩን፣ በከተማ የሚገኙ ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዳላቸው ምዘናዎቹ ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።

በሰለጠኑና ከፍ ያለ የትምህርት ደረጃ ባላቸው ርዕሰ መምህራን የሚመሩ ትምህርት ቤቶችና የተሻለ ደረጃ ያላቸው ትምህርት ቤቶች የተሻለ ውጤት ማሳየታቸውን 'ያረጋገጥንበት ዓመት ነው' ብለዋል ሚኒስትሩ።

በሁለተኛ ደረጃ በተለይም በ10ኛና 12ኛ ክፍል ተማሪዎች ላይ የተደረገው አገር አቀፍ ሳይንሳዊ ጥናት ውጤትም እጅግ ዝቅተኛ ሲሆን ውጤቱ እየተሻሻለ ሳይሆን እየተባባሰ ያለ ችግር ነው ብለዋል።

ከ2008 እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ በአገሪቱ የነበረው አለመረጋጋት፣ የመምህራን ብቃት፣ የትምህርት መሳሪያዎች አቅርቦት አለመሟላት፣ የትምህርት ቤት አመራሮች ብቃት ማነስ፣ የትምህርት ቤቶችና የማህበረሰቡ ግንኙነት አለመጠናከርም የችግሩ መንስኤዎች ናቸው።

ይህም በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ለማሳካት ከተያዘው እቅድ አንጻር አሳሳቢ በመሆኑ የመንግስት፣ የባለድርሻ አካላትና የወላጆችን ከፍተኛ ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑን ያመላከተ መሆኑን ተናግረዋል።

እነዚህና ከመምህራን ምልመላ፣ ስልጠናና ስምሪት ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያግዙ መፍትሄዎችን በማጥናት እየተዘጋጀ ባለው ፍኖተ ካርታ መካተታቸውንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም