ህዝቡ ትግሉን ወደ ኢኮኖሚው ማዞር አለበት - ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ

87

በደሌ መጋቢት 27/2011 ህዝቡ ከዚህ ቀደም ያደርግ የነበረውን ትግል ወደ ኢኮኖሚው በማዞር የኢኮኖሚ ትግል ማድረግ እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳን ጨምሮ ሌሎች የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ጋር በመሆን በቡኖ በደሌ ዞን በደሌ ከተማ ተገኝተው ከህዝብ ጋር ውይይት እያካሄዱ ይገኛሉ።

በመድረኩ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እንደተናገሩት፤ በአሁኑ ወቅት ትግል መደረግ ያለበትና ትኩረት መሰጠት ያለበት አገርን እንዴት መገንባት ይቻላል? በሚለው ላይ ነው።

የኦሮሞ ህዝብ የተለመደውን የአቃፊነት፣ አብሮ የመኖርና የመቻቻል ባህሉን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ህዝቡ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ጋር በመሆን ያደረገው ትግል ያመጣውን ለውጥ ለማስቀጠልመስራት እንዳለበት ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ''አሁን የምንሰራው ስራ ለትውልድ የሚተላለፍ መሆን አለበት'' ብለዋል።

''እስካሁን ችግር የሚፈጥሩ አካላትን እያሰርን፣ እየቀጣን አይደለም፤ በኦሮሞ ባህል መሰረት እየመከርንና እያስተማርን እንገኛለን'' በማለት መንግስት ችግሮችን ለመፍታት እያከናወነ ስላለው ተግባር አስረድተዋል።

የህግ የበላይነትን ማስከበርና ወደልማት መገባት እንዳለበት ገልጸው፤ ሁሉም ትኩረቱን ወደኢኮኖሚው ማዞር እንዳለበት አሳስበዋል።

መንግስት የኢትዮጵያን ህዝብ ኑሮ ለማሻሻል ባለፈው አንድ አመት በተሰራው ስራ በርካታ ለውጥ የመጣ መሆኑን ገልጸው አሁንም እየታዩ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የሚታዩት ችግሮችም በሂደት የሚፈቱና መፍትሄ የሚያገኙ መሆናቸውን አመልክተዋል።

''ኢትዮጵያ ለሁላችንም የምትበቃ አገር በመሆኗ በባህላችን መሰረት በመተሳሰብና በመፈቃቀር አብረን ወደፊት መጓዝ አለብን።'' ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ለውጡን ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገርና የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል ተግባር እየተከናወኑ እንደሆነ ተናግረዋል።

በኦሮሚያ ክልል የቡኖ በደሌ ዞን ዋና መቀመጫ የሆነችው በደሌ ከተማ ከአዲስ አበባ በ483 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኝ ሲሆን አካባቢው ለቡና እርሻ ምቹ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም