በፖለቲካው መስክ የተገኘውን ድል በኢኮኖሚው ዘርፍ ለመድገም እንሰራለን...የኦዲፓ አባላትና ደጋፊዎች

112

ነቀምቴ መጋቢት 26/2011 ከኦዲፓ አመራር ጎን በመቆም በፖለቲካው መስክ የተገኘውን ድል በኢኮኖሚው ዘርፍ ለመድገም እንደሚሰሩ አስተያየታቸውን የሰጡ የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች ገለጹ፡፡

ኦዲፓ የተመሰረተበትን 29ኛ ዓመት በዓል ዛሬ በዞኑ ሻምቡ ከተማ በከፍተኛ ድምቀት ተከብሯል፡፡

ከበዓሉ ተሳታፊዎች መካከል የሻምቡ ከተማ ነዋሪና የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መልኬ ጽዮን ቄሲስ ተፈራ ቢሻው እንዳሉት ባለፉት 29 ዓመታት ፓርቲው የተለያዩ ድሎችን አስመዝግቧል።

በክልሉ በፖለቲካው መስክ የተገኙትን አበረታች ድሎች በኢኮኖሚው ዘርፍ ለመድገም ከድርጅቱ ጎን በመቆም እንደሚንቀሳቀሱና ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ገልጸዋል። 

የኦሮሚያ ክልልና የዞኑ ሕዝብ ከመንግስት ጎን በመቆም የአካባቢውን ሰላም ለማስከበርና አገራዊ ልማትን ለማፋጠን የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊያደርግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የእምነቱ ተከታዮችም ለአገር አንድነትና ለሰላም ጠንክረው እንዲሰሩ በማድረግ የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡

የጮመን ጉዱሩ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ ዘነቡ ዳኜ በበኩላቸው "የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ለኦሮሞ ሕዝብ ነፃነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተ ደርጅት ነው" ብለዋል። 

"በፖለቲካ መስክ የተገኘውን ድል በመጠበቅ በቀጣይ የኢኮኖሚውን ዕድገት ለማፋጠን መላው የኦሮሞ ሕዝብ ከድርጅቱ ጎን መቆም ይኖርበታል" ብለዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት ኦዲፓ በተደራጀ መንገድ ባደረገው እንቅስቃሴ የኦሮሞን ሕዝብ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥያቄዎች የመለሱ በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገቡን ያስታወሱት ደግሞ የዞኑ ኦዲፓ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባይሳ ተመስገን ናቸው።

በቀጣይም ፓርቲው የኦሮሞን ሕዝብ አንድነት በማጠናከርና ከጎኑ በማሰለፍ በክልሉ ተጨማሪ ዘርፈ ብዙ ድሎችን ለማስመዝገብ እንደሚሰራ  አስታውቀዋል፡፡

ለፓርቲው ቀጣይ ስኬታማነት የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።

በበዓሉ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኦዲፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ የኦዲፓ የድል ምስጢር የሕዝቡ አንድነት፣ መደማመጥና መተባበር መሆኑን ገልጸዋል።

የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም የኦሮሞ ሕዝብ ከስሜት ተላቀው በሁሉም መስክ አንድነታቸውን በማጠናከር በፖለቲካው መስክ የተገኘውን ድል በኢኮኖሚውም ሊደግሙ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በተለይ የህዝቡን ኑሮ ለመለወጥ አባላትና ደጋፊዎቹ ቃላቸውን በማደስ ተግተው ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም