በትምህርት ተቋማት የስነ-ምግባር ትምህርት በትኩረት ይሰራበታል...የፌዴራል ስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን

168

ጎንደር መጋቢት 26/2011 በትምህርት ቤቶች የህጻናትና ወጣቶች የስነ-ምግባር ትምህርት ግንባታ በተጠናከረ መንገድ እንዲካሄድ በትኩረት እንደሚሰራ የፌደራል ስነ ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በሀገራችን ለ14ኛ ጊዜ የተከበረውን የአለም የጸረ-ሙስና ቀን ዛሬ በተለያዩ ዝግጅቶች አክብሯል፡፡

ከሚሽነር አየልኝ ሙሉአለም በበአሉ ላይ ተገኝተው እንደተናገሩት በስነ-ምግባር የታነጸ ትውልድ የነገ ሀገር ተረካቢ በመሆኑ ኮሚሽኑ ለስነ-ምግባር ትምህርት ግንባታ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል፡፡

ትውልድን በስነ-ምግባር ኮትኩቶ ለሃላፊነት ማብቃት የመጀመሪያው መሰረት ሊሆኑ የሚችሉት ትምህርት ቤቶች በመሆናቸው ኮሚሽኑ የአምስት አመት ስትራቴጂ መንደፉን ተናግረዋል፡፡

በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚተገበረው የህጻናትና የወጣቶች የስነ-ምግባር ትምህርት ከእውቀትና ክህሎት ባሻገር በአመለካከት ጭምር የተገነባ ዜጋ መፍጠርን አላማ ያደረገ ነው፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የስነ-ምግባርና የሙስና ችግሮችን ከስረ መሰረቱ መቅረፍ የሚያስችል በጥናት ላይ የተመሰረተ ግብአት በማቅረብ ኮሚሽኑን ሊደግፉ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዘዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን በበኩላቸው “ሙስና ስነ-ምግባር በጎደላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች የሚፈጸም ለሀገር እድገትና ልማት ጸር የሆነ ህገ-ወጥ ተግባር ነው”ብለዋል።

ሙስናን የሚጸየፍ ትውልድ ለመቅረጽ በሚደረገው ትግል ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው ቆይታቸው የሙስናን አስከፊነት ይበልጥ እንዲገነዘቡ የማድረግ ስራ በየአመቱ እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በዩኒቨርሲቲው የስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና መከታተያ ዳይሬክቶሬት ከማቋቋም ጀምሮ ለሙስና ተጋላጭ የስራ ክፍሎችን በጥናት በመለየት የማስተካከያ እርምጃዎች ሲወሰዱ መቆየታቸውንም ገልጸዋል።

የዩንቨርሲቲው የስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና መከታተያ ዳይሬክተር አቶ ካሳ ተሸመ በበኩላቸው “ባለፉት አመታት ከ25ሺህ ለሚበልጡ የዩኒቨርሲቲው ተመራቂዎች በስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና በባለሙያዎች የግንዛቤ ትምህርት ተሰጥቷል”ብለዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው ከአገልግሎት አሰጣጥ፤ ከመልካም አስተዳደር፤ ከሀብት አጠቃቀም ከግዢና ከጨረታ አሰራር አንጻር ለሙስና ተጋላጭ የሆኑ 10 የስራ ክፍሎች ላይ የዳሰሳ ጥናት እንደተካሔደም ተናግረዋል።

ከ576 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ስምንት የግንባታ ፕሮጀክቶች ጨረታቸው ከህግ አግባብ ውጪ በመሆኑ መሰረዛቸውን ገልጸው ሙስናን በማጋለጥ የመንግስት ሃብት እንዳይባክን የተከላከሉ 139 ሰራተኞችም የማበረታቻ ስርዓት ተጠቃሚ መደረጋቸውን ጠቁመዋል።

በበአሉ ላይ ከሀገሪቱ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ አመራሮች እንዲሁም ከፌደራልና ከክልል የስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን የመጡ የስራ ሃላፊዎችና የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት ተሳትፈዋል፡፡

ዩንቨርሲቲው እለቱን በጽዳት ዘመቻና በፓናል ውይይት ለ10ኛ ጊዜ በቅጥር ግቢው አክብሯል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም