የሲውዲን መንግስት ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለችውን የለውጥ ሂደት ለማጠናከር የ20 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ሊሰጥ ነው

108

አዲስ አበባ  መጋቢት 26/2011 የሲውዲን መንግስት የኢትዮጵያን የለውጥ ሂደት ለማጠናከር እንዲቻል  የ20 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለፀ።

ይህ የተገለፀው በኢትዮጵያ የሲውዲን አምባሳደር ቶርቢጆርን ፒተርሶን ከገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ አድማሱ ነበበ ጋር ዛሬ በተወያዩበት ወቅት ነው።

በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ተግባራዊ የሚሆነው የገንዘብ ድጋፍ አገራዊ የለውጥ ሂደቱን ከማገዝ ባሻገር የልማት ትብብሩን ለማሳደግና ለማጠናከር የሚያስችል መሆኑን ሚኒስትር ዲኤታው በዚሁ ወቅት አስታውቀዋል።   

በተለይም የመንግስት ተቋማትን ለማጠናከር፣ በዴሞክራሲና በሰብአዊ መብት ላይ የሚሰሩ የሲቪክ ማህበራትን አቅም ለማጎልበት የገንዘብ ድጋፉ ትልቅ ሚና አለው ነው ያሉት።

አገሪቱ በቀጣይ ለምታካሂደው ምርጫ፣ የፍትህ አካላትን ጨምሮ ለተለያዩ የአቅም ግንባታ ተግባራት እንዲሁም የሰብአዊ መብት ተሟች ተቋማትን ለመደገፍም እንዲሁ።

በኢትዮጵያ የሲውዲን አምባሳደር ቶርቢጆርን ፒተርሶን በበኩላቸው እንደገለፁት፤ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እያካሄደች ያለችን የለውጥ ሂደት ማጎልበት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ የሲውዲን መንግስት ያለውን አጋርነት ይቀጥላል።

በተለይም በዴሞክራሲ፣ በህግ የበላይነት፣ በሰብአዊ መብት ጉዳዮች ላይ ከመንግስትና ከሲቪክ ማህበራት ጋር ለውጡ በሚጠናክርባቸው ጉዳዮች ላይ በጋራ እንደሚሰሩም ገልጸዋል።

አገራቱ ወደፊትም ያላቸውን መልካም ግንኙነት በማጠናከር ትኩረትን በሚሹ ሌሎች የልማት ትብብር መስኮች ላይ በጋራ እንደሚሰሩም በዚሁ ወቅት ተመልክቷል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም