ረጲ የደረቅ ቆሻሻ ሃይል ማመንጫ ስራ ያቆመው የአየር ንብረትን መቋቋም በሚችል መልኩ ባለመሰራቱ ነው

96

አዲስ አበባ መጋቢት 26/2011 ኢትዮጵያ ለምትከተለው አረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ማሳያ ነው የተባለለት ረጲ የደረቅ ቆሻሻ ሃይል ማመንጫ ስራ ያቆመው የአየር ንብረትን መቋቋም በሚችል መልኩ ባለመሰራቱ ነው ተባለ።

የከተማዋን 80 በመቶ ደረቅ ቆሻሻ በመጠቀም 50 ሜጋ ዋት ሃይል ያመነጫል የተባለለት ይህ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ ለምትከተለው አረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ዋነኛ ማሳያ እንደሆነ ተገልጾ ነበር በምርቃት ስነ-ስርዓቱ ላይ።

የረጲ ደረቅ ቆሻሻ ሃይል ማመንጫ ከ2 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ለግንባታ ወጪ ተደርጎበት ከሁለት ዓመታት የግንባታ መዘግየት በኋላ ነሃሴ 13 ቀን 2010 ዓም መመረቁ ይታወሳል።

ግንባታውን ያከናወነው የእንግሊዙ ካምብሪጅ ኢንዱስትሪ ሃላፊነቱ የተወሰነ ኩባንያ ሲሆን በንዑስ ተቋራጭነት የቻይናው ኤሌክትሪክ ኢንጂነሪንግ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል የኮርፖሬት ፕላኒንግ ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ተስፋዬ ባቱ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳሉት ረጲ ደረቅ ቆሻሻ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሃይል ለማመንጨት ዝግጁ በመሆኑ መንግስት እንዲመረቅ ወስኗል።

ይሁንና ፕሮጀክቱ በአውሮፓ የጥራት ደረጃ የአየር ብክለትን መከላከል በሚችል ሁኔታ ባለመሰራቱ ስራውን እንዲያቆም ተደርጓል ነው ያሉት።

ግንባታውን በንዑስ ስራ ተቋራጭነት ያከናወነውየቻይናው ኤሌክትሪክ ኢንጂነሪንግ ፕሮጀክቱ በመመረቁ ቀሪ ስራዎችን ለመጨረስ ፈቃደኛ እንዳልነበርም ኢንጂነር ተስፋዬ ተናግረዋል።

ይሁንና በቻይና ኤምባሲ በኩል ከተቋራጩ ጋር መግባባት ላይ በመደረሱ ቀሪ ስራዎችን ለማከናወን ስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል።

በአሁን ጊዜ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም 95 በመቶ መሆኑንና ሃይል ማመንጨት ሲጀምር በቀን 1 ሺህ 400 ቶን ደረቅ ቆሻሻ በግብዓትነት ይጠቀማል።

በምረቃው ስነ-ስርዓት ላይ ተገኝተው የነበሩት የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ ለምትከተለው አረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ዋነኛ ማሳያ እንደሆነና ሌሎች የአፍሪካ አገሮችም ከዚህ መማር እንዳለባቸው ነበር የገለጹት።

በተመሳሳይ የአፈጻጸም ችግር የነበረባቸው የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ፈጥነው ወደ ስራ እንዲገቡ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ኢንጂነር ተስፋዬ አስታውቀዋል።

እንደ ኢንጂነር ተስፋዬ ገለጻ፣ በአንድ ዓመት ውስጥ ግንባታቸው ተጓትቶ የነበሩት የህዳሴ ግድብን ጨምሮ ገናሌ ዳዋና ረጲ ደረቅ ቆሻሻ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች በአፋጣኝ ወደ ሃይል ማመንጨት ስራ እንዲገቡ ርብርብ ተደርጓል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ሲሰራ የነበረው የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን(ሜቴክ) የፕሮጀክት ማኔጅመንት ክፍተት ግንባታው እንዲዘገይ ማድረጉን ያስታወሱት ኢንጂነሩ ለሌላ ስራ ተቋራጭ እንዲሰጥ በመደረጉ ፕሮጀክቱ በአሁኑ ወቅት ወደ ስራ እንዲገባ በማድረግ "የተቀዛቀዘውን የህዝቡን ስሜት ለመመለስ ጥረት እያደረግን ነው'' ብለዋል።

የገናሌ ዳዋ ሶስት የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫም ላለፉት ሶስት ዓመታት ተገንብቶ የተጠናቀቀ ቢሆንም ውሃ መያዝ አለመቻሉን ነው የገለጹት።

ለዚህ ደግሞ ዋነኛ ምክንያት ለአካባቢው ነዋሪዎች የሚከፈል የካሳ ክፍያ አለመኖሩን ነው።

የካሳ ክፍያው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱም ተቋሙ ክፍያውን መፈፀም የማይችልበት ደረጃ ደርሶ እንደነበር አስታውሰዋል።

የተቋሙ አመራሮች ፕሮጀክቱ ፈጥኖ ወደ ሃይል ማመንጨት እንዲገባ ከአካባቢው ነዋሪዎችና ከሃይማኖት አባቶች ጋር ውይይት በማድረግ ክፍያው እንዲፈጸም በወሰኑት መሰረት ግድቡ የካቲት 21 ቀን 2011 ዓ ም ውሃ የማቆር ስራ ተጀምሯል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም