የአገሪቱን ልማትና እድገት ለማስቀጠል የሚያስችል አገር አቀፍ የሰው ሃብት ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ መዘጋጀቱ ተጠቆመ

75
አዳማ ግንቦት 24/2010 የአገሪቱን ልማትና እድገት አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችል አገር አቀፍ የሰው ሃብት ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ ረቂቅ ሰነድ መዘጋጀቱን የፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስቴሩ በፖሊሲና ስትራቴጂው ላይ ግብዓት ለማሰባሰብ በአዳማ ከተማ ያዘጋጀው የውይይት መድረክ  ተጀምሯል። መድረኩን የመሩት የሰው ሃብት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አየለች እሸቴ እንደተናገሩት የሰው ሃብት ልማት ሥራው በፖሊሲና ስትራቴጂ ያልተመራ በመሆኑ የተለያዩ ችግሮች ተስተውሎበታል። በተለይ ከአገሪቱ ራዕይና የልማት ግቦች አንጻር ያልተቃኘ፣ የተበታተነና የማይናበብ መሆኑን በተካሄደ የዳሰሳ ጥናት መረጋገጡን ገልጸዋል። ይህንን ለማስተካከልና ዴሞክራሲያዊ አንድነትን ለማጎልበት፣ አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመፍጠር እንዲሁም የዕድገትና የልማት ግቦችን ለማሳካትና በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን አዲስ የሰው ሃብት ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ እንዲዘጋጅ ማስፈለጉን ተናግረዋል ። ከዚህ በተጨማሪ የሥራ ፈጠራን ከማጎልበት፣ መልካም አስተዳደርን ከማስፈን፣ ኪራይ ሰብሳቢነትን ከማክሰም አንጻር የሚስተዋለውን ክፍተት ለመሙላት የሚያስችል ፖሊሲና ስትራቴጂ መቅረጽ በማስፈለጉ መሆኑን አስረድተዋል። የተዘጋጀው የሰው ሃብት ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ ረቂቅ ሰነድ በመጀመሪያ ዙር ግብዓት እንዲሰጥበት መደረጉን ያስታወሱት ወይዘሮ አየለች፣ መደረኩም ከመላው አገሪቱ የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት አስተያየት እንዲሰጡበት ለማድረግ ታስቦ መዘጋጀቱን ገልጸዋል። የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ሚኒስትር አማካሪ አቶ ሽመልስ አበበ በበኩላቸው በሰው ሀብት ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ ቀረፃው ላይ ከተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ ከዩኒቨርሲቲዎችና ከአቅም መገንቢያ ተቋማት የተውጣጡ አካላት መሳተፋቸውን አስታውቀዋል። ፖሊሲና ስትራቴጂውን መቅረጽ ያስፈለገው መንግስት፣ ህዝቡንና የግል ዘርፉን በሰው ሃብት ልማቱ ለማካተት ሲባል መሆኑን ተናግረዋል። በተጨማሪም በአገሪቱ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት፣ ልማቱን በዘላቂነት ለማስቀጠልና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ የሰው ሃብት ለማፍራት እንዲቻል ታስቦ መሆኑን አስረድተዋል። የአገሪቱ ትምህርትና ስልጠና በልማታዊ አስተሳሰብና መርህ ላይ የተገነባ እንዲሆን፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮዽያውያንና ትውልደ ኢትዮዽያውያን ያካበቱትን አቅም በማካፈል ለአገራቸው ልማት ማበርከት እንዲችሉም ጭምር ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን አመልክተዋል። እንደ አቶ ሽመልስ ገለጻ ረቂቅ ሰነዱ በባለድርሻ አካላት ዳብሮ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከጸደቀ በኋላ ሥራ ላይ ይወላል ተብሎ ይጠበቃል። ለሦስት ቀናት በተዘጋጀው በዚህ መድረክ  ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት፣ የሃይማኖት አባቶችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም